Search This Blog

Sunday 30 July 2017

ደረቅ ጭንቅላት እንጂ ደረቅ አፈር የለም

መቀሌ ነው አሉ። አንድ አውደ ጥናት ተዘጋጅቶ አንድ ፕሮፌሰር ጥናት ያቀርባሉ። ጥናቱ እፀዋት ላይ ያተኮረ ሲሆን ፕሮፌሰሩ "የግራር ዛፍ ችግኝ ችግር ስላለብን በቀላሉ ማብቀል(ማባዛት) አልቻልንም" ብለው ይናገራሉ። በአውደ ጥናቱ የተጋበዘ አንድ አርሶ አደር እጁን ያወጣና እሱ በጣም ቀላል ነው እኔ ላሳያችሁ እችላለሁ ብሎ ይናገራል። ፕሮፌሰሩ አርሶ አደሩን ምን ታውቃለህ ዝም በል አይነት ንግግር ይናገሩታል። እልህ የያዘው አርሶ አደር
"መኪና መድቡና እኔ ማሳ ድረስ ይዣችሁ ልሄድ" ብሎ ይከራከራል። ተፈቅዶለት የአውደ ጥናቱን ተሳታፊዎች ጭምር ይዘው ወደ ማሳው ያመራሉ። አርሶ አደሩ ግራሩን ያራባበትን መንገድ በተግባር እያሳየ ገልፃ አደረገላቸው። በዚህ ግዜ ፕሮፌሰሩ የሚገቡበት ይጠፋቸዋል። በዚህ የተበቃሳጨው አርሶ አደር
"ደረቅ ጭንቅላት እንጂ ደረቅ አፈር የለም" ብሎ ፕሮፌሰሩን አስገባላቸው። ይህንን የነገሩን የአውደ ጥናቱ ተሳታፊ የነበሩ ናቸው።
እነ ዶክተር ፍቀደ አዘዘ በአንድ ወቅት ለጥናት ወደ ሰሜን ሸዋ ሄደው ይመስለኛል ለጥናቱ አርሶ አደሮች ይሰበስባሉ። " እንግዲህ ለጥናቱ ሰዎች ስንመርጥ 'በራንደም ሳምፕሊንግ' ነው።ከእናንተ ውስጥ ዝም ብለን አንዳንድ ሰው እንዳገኘን እንመርጣለን" ይሏቸዋል። አንዱ አርሶ አደር
" እና በብድግ ብድግ መረጣ ነው አትሉንም ወይ?" ብለው ተናግረው ይህንን ቃል ወደ ቋንቋው አስገብተው ሲጠቀሙበት እንደነበር የፎክሎር መምህራችን ሲያስተምረን ነግሮናል። ምን ለማለት ነው ማህበረሰቡ ጋር ትልቅ እውቀት አለ። ተማርን ብለን በያዝናት ወረቀት ከምንኮፈስ ለማህበረሰቡ እውቀት እውቅና እየሰጠን መስራት ይኖርብናል። አርሶ አደሩ ጋር ተዝቆ የማያልቅ እውቀት አለ። ከአንድ የህክምና ዶክተር በተሻለ የባህል መድሃኒተኞች ስለ በሽታ እና መድሃኒት የተሻለ እውቀት አላቸው፣ ከታሪክ ባለሙያዎች ባልተናነሰ መልኩ ሽማግሌዎት የማያልቅ ታሪክ ያውቃሉ፣ ከግብርና ባለሙያ በተሻለ አርሶ አደሮች ስለ ምርት እና አፈር ምንነት ያውቃሉ። ልየነቱ ቀለም የማወቅ እና ያለማወቅ ጉዳይ ካልሆነ በቀር።

አብዲሳ አጋ

እጅ እና እግሬን የፊጥኝ አስረው ከፎቅ ላይ ወረወሩኝ። በታዕምር ተረፍኩ። ፓሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ። ውሃ በላየ ላይ እያፈሰሱ እስኪበቃቸው ደበደቡኝ። ውሃውን በላየ ላይ ለቀውት ሲፈስብኝ አደረ።በዚያ ላይ መሬቱ ሲቢንቶ ነበር። ጠዋት ሲመጡ "ይሄ ጥቁር አልሞተም" ብለው በመስኮት አይተውኝ ይሄዳሉ። የህዝቡ መገደል የአላግባብ ደም መፍሰስ ያሳዘነኛል። ይቆጨኛል። ከአዲስ አበባ ሞቃዲሾ፤ ከሞቃዲሾ ጣልያን ናፓሊ በመርከብ ነው የሄድንው። ናፓሊ ውስጥ አኛ የሚባል እስር ቤት ገባን። ተለይቶ የተዘጋጀ ቦታ ነው። እዚያ ሆነን የእንግሊዝ መንግስት ወረቀት ይበትን ነበር። የእነ ሃይለስላሴን፣ሩዝቬልት፣ናፓሊን እና የመሳሰሉትን መሪዎች ስም የያዘ ነው። ይህንን ወረቀት ይዟል ተብየ ሰደበደብ መሞቴ ካልቀረ ብየ ወታደሩን መልሼ መታሁት። ይሄ ነው ከፍተኛ ድብደባ የዳረገኝ።
ስር ቤት እያለሁ ለማምለጥ ከፍተኛ ጉጉት ነበረኝ። ጁሌት የሚባል ዩግዝላቪያዊ ጓደኛየም ይህንን ያስብ ኖሯል። 3ኛ ፎቅ ላይ ነበር የታሰርኩት። አንድ ቀን አቅሮፕላን መጥቶ ሲደበድብ አጋጣሚውን አግኝተን በመብራቱ ታግዘን ከ3ኛ ፎቅ ብርድ ልብስ ቀድጄ በእሱ ወርጄ ከጄሌት ጋር አመለጥን። ወደ ሳንቢችኖ ተራራ ለመድረስ ስንጓዝ አደርን። በማግስቱ ደረስን። በኋላ እንግሊዛዊው አዛዥ ሜጄር ፋይልን
"እዚያ ብዙ ኢትዮጵያኖች እና ዩጎዝላቪያን እስረኞች አሉ እነሱን ማስፈታት እንፈልጋለን። እነሱን እናስለቅቅና መሳሪያም እንዝረፍ " ብለን መሳሪያ እንዲሰጠን ጠየቅን።
" ይሄ ይፈፀማል ብየ አለምንም ግን ውሰዱ" ተብለን ተፈቀደልን። እዚያ ከነበሩት ኢትዮጵያዊያን እንግሊዛዊያን እና ዩጎዝላቪያን ውስጥ 30ዎቹ ወደ እስር ቤት ሰበራው ለመሄድ ተስማሙ። እጃችን ላይ የነበረው መሳሪያ 1ሳንጃ፣ አንድ አልቤን ክላሽ፣አንድ የእጅ ቦንብ እና 2ክላሽ ነው። እስር ቤቱ 75ኬ.ሜ አካባቢ ይርቃል። እስር ቤቱ ለመድረስ ትንሽ ሲቀረን እና ትሬያ የምትባል ከተማ ስንደርስ ስልክ እና መብራት እንዲቆረጥ አደረግን። እስር ቤቱ ደረስን። እኔ እና ዱገላስ በደረታችን ተስበን ወደ ዘቡ ስንጠጋ ዘቡ በቁሙ እንቅልፍ ይዞት አየን። ዱገላስ በተክለ ሰውነት ገዘፍ ስለሚል አንገቱን ሲይዝልኝ እኔ ጠመንጃውን እና እግሩን ይዤ ወደ ጉድጓድ ውስጥ ወስደን ገደልንው። ዱገላስ የዘቡን ልብስ ለብሶ እንዲቆም አደረግን። ሌላ ዘብ ደግሞ ለቅያሬ መጣ። ያንንም ዘብ ገላገልንው። ሌላኛውን ዘብ ያዝንና መሳሪያችንን ወደ 3 ከፍ አደረግንው። ዘብ ቤት ሄደን የሁሉንም መሳሪያ ወሰድን። አንደኛውን ዘብ "የወህኒ ቤቱ ሃላፊ ወዳለበት ቦታ ውሰድን" አልንው። አማራጭ ስላልነበረው ወሰደን። ማርሻል ሎጄስቴሬኢያሪኮ ይባላል።
"ማርሻል" ብሎ ተጣራ።
"አቤት" አለው
"ከታች ብዙ ድምፅ ይሰማኛል ምንድነው?" አለው
"መብራትም ጠፍቷል ምን ይሆን" ብሎ ተነሳ። ብቅ ሲል በመትረየስ መታሁና ጣልኩት። ሚስቱ እና ልጆቹ መንጫጫት ሲጀምሩ እነሱንም ጭረስናቸው። እስረኞቹን በሙሉ አስፈታናቸው። ምግብ፣ ልብስ እና በርካታ መሳሪያዎችን ዘረፍን እና መሄድ የፈለጉትን እስረኞች ይዘን ወደ ቦታችን ተመለስን።
.....አንድ ቀን የጀርመን ናዚ ወታደሮች በአውሮፕላን እኛ ከሰፈርንበት ቪያኖራ ቦታ አረፉ። ቦታውን ለመሰለል ኖራል የመጡት። አንዱን ያዝንው እና ሁሉቱን አውሮችላናቸውን አስነስተው አመለጡን። የተያዘውን ሰው ምርመራ አደረግንበት።ዮጎዝላቪያዊው ሜጀር ጁሌት ጀርመንኛ ጥሩ አድርገጎ ይናገር ስለነበር የመጡበትን ምክንያት ጠየቀ።
"እዚህ ቦታ አርበኞች ስላሉ እነሱ ያሉበትን ቦታ አይተን በሌላ ግዜ በእግረኛና በአውሮፕላን ለመደብደብ ነው ብሎ" ይመልሳል። "ይሄ ፍርድ ያስፈልገዋልና ፍርድ መሰጠት አለበት" ብለን ወሰንን። እንግሊዛዊው ሜጀር ፋይል እንዲደበደብ አዘዙ። የምትፈልገውን ተናገር ሲባል
"አንደኛ በሌላ ሰው እጅ እንዳልደበደብ በኢትዮጵያዊው አንቶኒ(አብዲሳ) እጅ መሞት እፈልጋለሁ።ሁለተኛ መሳሪያየን ለእሱ መታሰቢያ ስጡልኝ" ብሎ ተነገረ። ከዚያ ደግሞ "አንድ ቃል ልናገር ብሎ መንግስቴ ለዘላለም ይኑርልኝ" ብየ ልናገር ብሎ ተፈቀደለት።
..... ድል አድርገን ሮም ስንገባ 400 ወታደሮች ሁሉም የውጭ ሃገር ዜጎች ናቸው የእንግሊዝን ባንዲራ በቀኝ ክንዳቸው የኢትዮጵያን ባንዲራ በግራ ክንዳቸው ላይ እንዲያስሩ አደረኩ። እኔ የምፈልገው የኢትዮጵያ ቀለም እዚያ መገኘቱን ነበር።
..... እዚያ በእኔ ስም ሽፍቶች ሃገሬውን ይዘረፉ ነበር። ተከታትየ በህይወታቸው ቀጣኋቸው።
...... እዚያ ሆኜ እናቴም አባቴም ወንድሞቼም አይደሉም የሚናፍቁኝ። ሃገሬ ብቻ ነበረ የሚናፍቀኝ። ሃገሬ ነው
አብዲሳ አጋ ከኢትዮጵያ ራዲዩ ጋር ካደረጉት ቃለመጠይቅ የተወሰደ
"አንሶላ የተጋፈፍኳቸውን ሴቶች ቁጥር አላስታውስም። ቆንጆ ከሆነች እንድታመልጠኝ አልፈልግም። ሁሉም ቆንጆ ሴቶች ሚስቶቼ ቢሆኑ እመኛለሁ። በተለይ ይሄ የሹፍርና ስራየ ቀላል አልተመቸኝም። ማርሽ አስገብቼ እጄን ጋቢና ካስቀመጥኳት ልጅ ጭን ላይ ጣል አደርገዋለሁ። ዝም ካለች ጨዋታው ይቀጥላል። ካላለች ሌሎች ስልቶች ይከተላሉ።" አለኝ በታሪፍ ተጣልተን በኋላ ምርጥ ጓደኛሞች የሆንን አንድ ሹፌር። ጋቢና ሰው አለ ሲል ቆይቶ ሊሞላ አንድ ሰው ሲቀር ደርሼ ነው ያስገባኝ። "ምን እንደሚያስጠልኝ ታውቃለህ?" አለኝ።
"አላውቅም" አልኩት።
"ሌዘር የሚለብስና ሳምሶናይት ቦርሳ የሚይዝ ሰው" አለኝ። ፈገግ አልኩለት እና
"ለምን"አልኩት።
"በቃ አጉል መብቴ ይከበር ባይ ናቸው። የእኛ ስራ ውጣ ውረዱ አይታያቸውም። በጣም ስለሚያበሳጩኝ እንደዚያ ያሉ ሰዎችን አልጭንም" አለኝ።
"ስራችሁማ ምን ውጣ ውረድ አለው። የፈለካትን ሴት እያሳደድክበት.." አልኩትና ሳልጨርስ አቋረጠኝ
"እሱስ ልክ ነሽ አባየ! ስንቱን በላንበት መሰለሽ። ጥቅሙ ይሄ ብቻ ነው። እንጂማ ትራፊክ በያዘህ ቁጥር የቀን አበልህን ለመንግስት እየገበርክ እንዴት ትችለዋለህ?" አለኝ።
"ዛሬ ግን ጋቢና ቆንጆ ሴት ባለመጫንህ ቅር አላለህም?" አልኩት።
"ቀላል ብሎኛል! ሴቶች በጣም ነው ደስ የሚሉኝ። ደግሞ መሪ የያዘ ወንድ በጣም ይወዳሉ። እኔማ ጋቢና ሴት ካስቀመጥኩ ችግር አለብኝ። ለምን ትልቅ ሰው አትሆን መነካካቴን አልተውም። አንድ ግዜ ወደ ደሴ ስንሄድ መሽቶ ሁሉም ተሳፋሪዎች እንቅልፍ ያዛቸው። ጋቢና የተቀመጠችውን ሴት ነካክቻታለሁ። እጄን ማርሽ እየቀየርኩበት አስመስየ ጡቶቿን ሳይቀር አሸሁላት። እሷም የምትሆነውን አሳጣት። ቀስ ብየ መኪናውን ዳር አስይዤ አቆምኩትና ለሽንት እንደሚወርድ ሰው ወረድኩ። እሷም ገብቷታል ወረደች። በጀርባ በኩል ስዞር ሰዎቹ ከእንቅልፋቸው እየነቁ የመኪናው መቆም ግራ ገብቷቸው መጋረጃውን ገለጥ ገለጥ ማድረግ ጀመሩ። በብስጭት ገብቼ መኪናየን መንዳት ጀመርኩ" ብሎ መሪውን በመዳፉ መታ አደረገው። ሲያወራ እያዝናናኝ መጣ። ስሜቱን በጭራሽ መደበቅ አይችልም። ሲበዛ ግልፅ ነው። ወሬው ደግሞ ከሴትና ወንድ ወሬ እንዲወጣበት አይፈልግም።
"አንድ ግዜ ደግሞ ባልና ሚስቶች ኮንትራት አድርሰኝ ብለውኝ ጉዞ ጀመርን። ጋቢና መጥተው ሁለቱም ተቀመጡ። ልጅቷ እንዴታባቷ እንደምታምር አትጠይቀኝ። ረዳቴ ከኋላ ወንበር ሄዶ ተኝቷል። ቀኑ እየመሸ ሲሄድ ባልዮው እንቅልፍ አዳፋውና ከኋላ ልተኛ ብሎ ሄደ። ረዳቱ ቦታ ለቀቀለትና አስተካክሎ አስተኛው። ረዳቴ ጋቢና መጥቶ ልጅቷን መሃል አስቀምጥናት። አባየ.. ጨዋታው ተጀመረ። ልጅቷን ከጭኖቿ ጀምሬ ስደባብሳት ፈፅሞ ልትከለክለኝ አልዳዳታም። ረዳቴም ይነካካ ኖሮ ዝልፍልፍ ማለት ጀመረች። ቆይቼ ረዳቱን አስትቼ ነገሩን ጋብ አደረግንው። አንዲት ከተማ ደረስን። መኪናውን ጥግ አስይዘን እራት እንደሚበላ ሰው ሆቴል ገባን።.."
ወሬውን እንደቀጠለ ስልኬ ድንገት ጠራ። ይህንን እያወራኝ ስልክ አንስቶ ነገር ማቆርፈድ መስሎ ቢታየኝም የስራ ስልክ ስለሆነ ማንሳት ግዴታ ሆነብኝ።
"ሄሎ"
"ደህና ዋልክ አዲስ ማታ ስራ መግባት አለብህ" ተባልኩ። መመለስ አለብኝ ማለት ነው።
"ሹፌር ስራ ገጠመኝ ወደ አዲስ አበባ ልመለስ ነው። መኪና አስቁምልኝ" አልኩት። መኪና አስቁሞልኝ ወደ አዲስ አበባ ጉዞየን ጀመርኩ። የልጁ ድርጊት ግን ከአዕምሮየ ሊወጣ አልቻለም።...

"አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት እያድር ይፋጃል እንደ እግር እሳት"

"አባቴ ሰይጣንን የሚያመልክበት ጎጆ ቤት ነበረው። የሆነ ወቅት ላይ ቤቷ ፈረሰች። ሰይጣንም አባቴን ቤቴን ካልሰራህልኝ ደመራን አላሳልፍህም እግድልሃለሁ አለው። አባቴ ነገሬ ሳይለው ተወው። እንደተባለው አባቴ ሆዴን ወጋኝ ብሎ ከዚህ ዓለም ተለየን። በዚያው ሳምንት እናቴም ሆዴን አመመኝ ብላ ለሞት በቃች። እኔ፣እህቴ እና ወንድሜም የትም ተበተንን። የምንበላው እና የምንለብሰውን ሰዎች እየመፀወቱን በነፍስ ለመቆየት ያክል እንኖራለን" አለች እና እንባዋ ዝርግፍ ብሎ ወረደ። ያሳዝናሉ። ኑሯቸው ከመቃብር በታች የሆነ ያክል ነው። እነዚህ ልጆች የሚኖሩት ከደብረ በረሃን በግምት 25ኪ.ሜ ከምትርቅ ቀይት ከምትባል ከተማ ውስጥ ነው። ምግባቸውን መምህራን በየተራ እያመጡ ይሰጧቸዋል። ለዚያውም ካልሰለቹ!! ከደሞዛችን ያዋጣናትን እና Hirut Negesue ሂሩት ነገሰ ሰብስባ የላከችልንን ገንዘብ ከፋፍለን የ2ወር ቀለብ እንዲገዛላቸው አደረግን። ሆድ እየጮኽ ትምህርት እና ለውጥ እንዴት ሊታሰብ ይችላል? ልጆቹ ይቺ ተደረገችልን ብለው ፈጣሪ ከሰማይ የወረደላቸው ያክል ተደሰቱ። አንጀት ይበላሉ።
ጓደኞቻችን Misahun Negash እና ይርጉ ኃይለማሪያም የመለመሏቸው ሌሎች ችግረኞች ቤት ሄድን። ከዚችው ከተማ * ኪ.ሜ አካባቢ ወደሚርቅ እና አዲስጌ ወደሚባል ቀበሌ። እዚህም ሌላ ችግር በሰዎች ላይ አፉን ከፍቶባቸዋል። እዚህ ቤት አንድ ልጃቸው ችግር አስመርሯት ወልዳ አራስ ልጇን ትታ በገመድ ታንቃ ሞተች። እናት ከሃዘን እና ከችግር ጋር የልጅ ልጇን ማሳደግ ተፈረደባት። የወላድ አንጀት ይሄን እንዴት ይቻል?
"አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት
እያድር ይፋጃል እንደ እግር እሳት" የሚለውን ግጥም አስታወስኩትና አጥንቴን ሰርስሮት ገባ። ችግር እና መጎሳቆል ሰው ፊት ላይ ሲነበብ ማየት ህመሙ ከተቸገሩት ሰዎች የሚተናነስ አይመስለኝም። ቤት መኪና ምናምን መመኘቴን እርግፍፍ አድርጌ ተውኩት። የችግራቸውን ሁኔታ አንድ በአንድ ነግሬ ሌላ ሃዘን እንድጨምርባችሁ ስለማልፈልግ ልዝለለው። ብቻ እዚህ ቤትም ትንሽ ነገር ተደረገችልን ብለው እንባ ተናነቃቸው። ገንዘቡን ለመስጠት ስንሄድ የቀበሌውን አስተዳዳሪ እንዲገኝ አድርገን ስለነበር ነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የድጋፍ ፍቃድ እንዲሚሰጧቸው እና የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው እንደሚችሉም ቃል ገቡልን። እኛ በሰበሰብናት ሚጥጥየ ገንዘብ ሰዎችን ማነሳሳት መቻላችን ትልቁ ግብ አደረገን ወሰድንው። እዚያው ወረዳ ላይ ሙሽ የሚባል ቀበሌ ላይም ሌላ ችግር ያነወዘው ቤተሰብም ጎበኘን። የሚያሳዝነው ሁሉም ቤት ልጆቹ ሲመረጡ የአካል ጉዳት እና ሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮች ያለባቸው ልጆች ነበሩ። የሆነው ሆኖ ባይጠቅምም ወገን አለን ብለው እንዲያስቡ ያደረግናቸው ይመስለኛል። እኛ ገንዘብ ኖሮን አይደለም ይህንን ያደረግንው። ብዙዎቻችን ከቤት ኪራይ የሚያልፍ ደሞዝ የለንም። ስንሰባሰብም ከደሞዛችን በወር 1መቶ ብር ብንለግሳቸው ብለን ነው። ይበዛብናል ሳንልስ እንቀራለን!? ከሁሉ ነገር የሚበልጥ ሰውን የመርዳት ወኔ ግን ነበረን። እነዚህ ልጆች ትንሽየ ከተማ ውስጥ ለቤት ኪራይ በወር 30 ብር የሚሰጣቸው ሰው ከምንም በላያቸው ነው። ከተማ ውስጥ ጎዳና የወጡ ሰዎች እኮ በቀን እጁን የሚዘረጋላቸው ሰው አያጡም። ገጠር ውስጥ ያሉት ግን ስለመኖራቸውም አይታወቁም። ተራፊ የሚሰጣቸው አይኖርም። የአብዛኛው ህዝብ አኗኗር ከዚህ ጋር የሚቀራረብ ቢሆንም እጅግ የባሱትን ማየት ሁሉ ነገር ውሸት መሆኑን ማንም ሰው ይረዳል። በቃ አሁንም ድሃ ነን። እልም ያልን ድሃዎች። የሆነው ሆኖ ቀጣይ ፕሮግራም ይኖረናል። ባናግዛችሁ እንኳ የልጆቹን አኗኗር አይተን በሃሳብም ቢሆን እንረዳዳለን የምትሉ ካላችሁ ቀጣይ ላይ አብረን ተጉዘን ኑሯቸውን አይተን መመለስ እንችላለን። ከአዲስ አበባ ደርሶ መልስ 120 ብር ቢፈጅ ነው። ሰዎች ያድርጉ ከማለት እኛም ትንሽየ ነገር ብናደርግ የአዕምሮ እርካታ ነው፤የማህበረሰብ ድጋፍ ነው፣የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ነው፤ህዝብ መውደድ ነው፤ህዝብን መውደድ ደግሞ ሃገርን መውደድ ነው። ህዝባችንን ሳንወድ እና ማገዝ እየቻልን ባናግዛቸው ሃገሬን እወዳለሁ ብንል ትርጉሙስ ምንድነው? አድራሻችሁን ብታስቀምጡልን አንድ ቀን በሚኖረን የደርሶ መልስ ጉዞ አብረን መጓዝ እንችላለን!!
#ሼር ብታደርጉና ለወዳጆቻችሁ ብታደርሱልን ደጋግ ሰዎችን እንድናገኝ ያግዘናል። እናንተም ይህንን ስታደርጉ ሰዎቹን እንደረዳችኋቸው ቁጠሩት።
መልካም ግዜ
8የደብረ ብረሀን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አባይ ባንኮችን ይሄዱና የደንበኞቻችሁን ገንዘብ የምታንቀሳቅሱበት ሲስተም ለዝርፊያ በቀላሉ ይጋለጣልና እኛ ደህንነቱን የሚያስጠብቅላችሁ ሲስተም እንዘርጋላችሁ ይሏቸዋል። "አሁን እናንተ.." በሚል አንፈልግም ይሏቸዋል። ልጆቹ "ለምን አናሳያችሁም" ብለው ሲስተሙን ሰብረው 80ሺ ብር አውጥተው ይጠቀሙበታል(ተመቹኝ)። በዚህ ምክንያት ልጆቹ በቁጥጥር ስር ዋሉ። እኔ ግን እነዚህን ልጆች ከማሰር እውቀታቸውን መጠቀም የሚሻል ይመስለኛል። በነገራችን ላይ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ እሳት የላሱ ልጆች ሞልተዋል። አንደኛው ልጅ የግዕዝ አማርኛ መተርጎሚያ ሶፍትዌር አዳብሯል። ቀጣይ አመት ወደ ስራ ሊያስገባው እየሰራ ነው። ሌላው ደግሞ ከአፈር ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚያስችል ስራ ሰርቷን። አንዱ የፊዚክስ መምህር ደግሞ ሊባረሩ ጫፍ የደረሱ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስጠናት ለውጤት አብቅቶ ከልጆቹ ጋር በመሆን ከቆሻሻ ከሰል እያመረተ ነው።
ሌላ ደግሞ እዚያው ደብረ ብረሃን የሆነውን ልንገራችሁማ.....
ልጁ ሹፌር ነው። ማንም የሚቀጥረው ሰው ያጣል። በመሃል አባቱ በጠና ይታመማሉ። ስለዚህ ያለኝ አማራጭ ብር መስረቅ ነው ብሎ ወደ አካሉ ሆቴል ያመራል። ይገባና 11ሺ 300 ብር ይዘርፍና ሊያመልጥ ሲል ፓሊሶች ይከቡታል። ጥበቡን ተጠቅሞ ተሰወረባቸው። ፓሊሶቹ ሆቴል ገብተው ፍለጋውን አጧጧፉት። ልጁ የለም። ከደቂቃዎች ፍለጋ በኋላ አንደኛው ግድግዳው ጥግ ያለውን ነጭ ነገር ከፈተው። አጅሬ 11ሺ 300 ብሩን እና ቢራ ታቅፎ ከተጋደመው ፍሪጅ ውስጥ ጥቅልል ብሎ ተኝቶ ኖሯል። አስቡት በደብረ ብረሃን ብርድ ፍሪጅ ውስጥ ገብቶ በረዶ ሸፍኖት አለመጥፋቱ!? ልጁን ወዳጄ alayu geremew አግኝቶ ሲያናግረው "አባቴን ለማዳን ስል ስርቆት ውስጥ በመግባቴ እና ስሰርቅ በመያዜ አልፀፀትም" ብሎታል።

ከቴም እቴ

ከስራ ስወጣ ወደ ቤት የሚሸኘኝ ሹፌር ካለወትሮው ሌላ መንገድ መርጦ ውስብስብ ያለ ሰፈር ውስጥ ይዞኝ ገባ። ለምን እንደሆነ ስጠይቀው "እቃ ተቀብለን ወደ ቤት ላደርስህ ነው" አለኝ። ተስማማን። ወደ ሰፈር ልንደርስ ስንል ቁልቁለት ነገር ኑሮት እንደገና ዳገት ያለው ቦታ ገጠመን። ይቺን ለመውጣት ከታች መንደርደር ያስፍፈልጋል። ቁልቁለቷን ጨርሰን ዳገቷን ስንጀምር የመኪናው ሞተር ድርግም ብሎ ጠፋ እና ሚኪናው ወደ ኋላ ተመለሰ። ሞተር አስነስቶ አሁንም ሊንደረደር ሲል ሞተር ይጠፋበት ጀመር። በ3ኛው ሲወጣ የሼፌሩን እግር ፔዳል አረጋገጥ ማየት ጀመርኩ። ዳገቱን ሲጀምር ፍሪሲዮን ሳይረግጥ ፍሬን ቶሎ ሲይዝ እና ሞተሩ ጠፍቶ መኪናው ወደ ኋላ ሲመለስ አየሁ። ይሄ ጠፍቶት ነው ብየ ባላስብም "ውረድ እና እኔ ላስጣልህ" አልኩት። አይሆንም ብሎ ድርቅ አለ። "
እንዲያውም አንተም ስለደረስክ በእግርህ ወደቤት ሂድና ምሳህን ብላ እኔም መኪናውን ወደ ኋላ ወስጄ ጥግ አስይዤ እቃየን ልቀበል" አለኝ። ነገሩ ሁላ ባያሳምነኝም ተስማማሁ። ዳገቷን ወጣ ብየ ወደ ቤት መግቢያየ እጥፍ ስል ከየት መጡ ሳልላቸው የሆኑ ሰዎች አፋፍሰው መኪና ውስጥ አስገቡኝ። መጀመሪያ በጃኬታቸው አይኔን ሸፍነውኝ ነበር። መኪና ውስጥ በሆነ ጨርቅ ነገር አይኔን ብቻ አስሩና እጄን ወደ ኋላ በካቴና ነገር አሰሩኝ።አንዳቸውንም ማየት አልቻልኩም።
"ስንነግርህ አልሰማ አልክ አይደል?" አለኝ አንደኛው። መኪናው እየሄደ ነው። ወዴት አቅጣጫ እንደሚሄድ መለየት አልቻልኩም።
"እንዴየ ምን አደረኩ ቆይ? ምን ነግራችሁኛል? ልትዘርፉኝ ከሆነ ያው ያለውን ውሰዱና እኔን ልቀቁኝ" አልኩ ልቤ እየመታ።
"ሂድ!! የማትረባ። አንተ አሁን ምን ኖሮህ ነው የምንሰርቅህ?" አለኝ።
"ከአንዴም ሁለት ግዜ ሰው ላክንብህ። አንተ ግን አሻፈረኝ አልክ" አለችኝ አንዷ ሴት።
"ስለምንድነው የምታወሩት"ብየ ተበሳጨሁ።
"እሱን ስትገረፍ ታውቀዋለህ" አለኝ ከጋቢና በኩል የተቀመጠ ሰው፡ ሹፌሩ ይሁን አይሁን ግን መለየት አልቻልኩም። ወዴት እየወሰዱኝ እንደሆን ለመለየት ጥረት ባደርግም አልተሳካልኝም።
"አራት ኪሎ፤ አራት ኪሎ፤ ቦሌ፤ ቦሌ የሚል የወያላ ድምፅ ሰማሁ። ወዲያው መስኮቶቹን ሲዘጉብኝ ድምፅ መስማት ሳልችል ቀረሁ።
"እናታችሁን ልቀቁኝ" ብየ እሪታየን ሳቀልጠው አንዱ
"ዝም በል ክፍት አፍ" ብሎ ጨርቅ አምጥቶ አፌ ላይ ወተፈብኝ። እግራቸው ማስቀመጫ ጋር አስተኙኝና እግራቸውን አስቀምጡብኝ። የአንደኛው ሰው እግር ሸተተኝ። ወደ ላይ ልበልህ አለኝ። አፌ ታፍኖላልና በደንብ በማይሰማ ድምፅ
"እናትህንና ጫማህ ይሸታል" አልኩት ለመገላበጥ እየሞከርኩ። እንደመሳቅ አሉና
"ገና የሽንት ቤት ቀዳዳ ውስጥ አንገትክን አስገብቼ እረግጥሃለሁ" አለኝ። በጫማው ቆሻሻ ረግጦ ኖሮ
"ወርደህ ጥርገህ ና" ምናምን አሉት።
"ስንደርስ በዚህ በማይረባ ሰው ጃኬት እጠርገዋለሁ" አለ። መናገር አልቻልኩም። ምን እየተሰራ እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም። እንኳን ለማምለጥ ለመጮህ እንኳ እንዳልችል አድርገውኛል። ሹፌራችን እጁ እንዳለበት ጠረጠርኩ። ከቢሮ ስንወጣ ሌሎች ሰራተኞችን እግረ መንገዱን ይዞ ይወጣ የነበረ መኪና ማንንም መጫን ሳይፈልግ እኔን ብቻ ይዞኝ እንዴት ሊወጣ እንደቻለ ግራ ገባኝ። መንገዳችን ላይ ይወርድ የነበረ ሰውም "ይዘህኝ ሂድ" ብሎት "ወደ ሌላ ቦታ ነው የምንሄደው" ብሎ እምብይ ብሏል። የተቀነባበረ ነገር እንዳለ ገባኝ። እንዴት እንዲህ አሳልፎ ይሰጠኛል? ዝም ብየ ማሰላሰል ጀመርኩ። አወጣለሁ አወርዳለሁ፥ ምንም ጠብ የሚል ሃሳብ ጠፋ። ይልቁንም ቀኑ የተወለድኩበት ቀን መሆኑ የባሰ አባሳጨኝ። መኪናው የሚያንገራግጭ መንገድ ውስጥ ገብቶ 5 ደቂቃ ያክል ከተጓዘ በኋላ አንድ ግቢ ውስጥ ገባ።
"አውርዱት" አለ መኪና ውስጥ ያልነበረ ሰው ይመስለኛል። አውረደውኝ ግራና ቀኝ ይዘው ፀጥ ወዳለ ቤት ውስጥ ይዘውኝ ገቡ።
"መጀመሪያ ይገረፍ ወይስ ቃሉን ይስጥ?" አለ አንደኛው።
"ሱሪውን አውልቀን እንግረፈው" አለች አንዲት ሴት። 'ድሮም ሴት አይሆነኝ ወይኔ ጉዴ አለቀልኝ በቃ' አልኩ በውስጤ። አፌ ውስጥ ጨርቅ ተወትፎ "ምን አድርጌ ነው ማለት እንኳ አልቻልኩም።
"ከአፉ ላይ የወተፋችሁትን ጨርቅ አውጡለት" አለ። የአብዛኞቹ ተናጋሪዎች ድምፃቸው ጎርነን ያለ ነው። ሆን ተብሎ የተደረገ እስኪመስል።
"የህዳሴው ግድብ ከዳር እንዳይደርስ ከግብፅ ጋር አሲረሃል" አለቸኝ ያቺ ቅልብልብ። ልክ ቲያትር እንደሚሰራ ድምፁዋን የሆነን ሰው ለማስመሰል የሞከረች ትመስላለች። ከት ብየ መሳቅ ስጀምር በጥፊ አጋየችኝ።
"እናትሽ ት..." ብየ ጮኩባት። በውስጤ 'ይሄ አጉል ልማድ' ብየ በስድቤ ተፀፀትኩ። 'በቅሎ ማስሪያዋን በጠሰች ቢሏት ወዲያው አሳጠረች' ብየም ተረትኩ።
"እግሩን ወደ ላይ አድርጋችሁ ስቀሉልኝ" አለ አንደኛው።
"ቆይ ቆይ መጀመሪያ የኢሜል እና የፌስ ቡክ አካውንቱን ከነፓስወርዱ ይስጠን" አለና ወረቀት ማገላበጥ ጀመረ።
"ኢሜልክን ተናገር" አለኝ።
" እናንተ ማን ናችሁና ነው የምነግራችሁ?"
"ሰውነትህ እንዲተለተል ከፈለክ አለመናገር መብትህ ነው" አለና አንባረቀ። ወዲያው
"አንተ ልብሱን አውልቅልኝ። አንቺ አልንጋውን አምጪ" ብሎ አዘዘ። ደንዝዣለሁ። አንደኛው መጥቶ ጃኬቴን እና ቲሼርቴን አወለቀ።
"እሺ እሺ ልስጣችሁ" ብየ ተስማማሁ።
"ኢሜልክን ተናገር አለኝ"
"addismekonen@yahoo.com" አልኩት።
"ፓስዎርድ" አለኝ። ሳልመልስ ዝም አልኩ
"ተናገር እንጂ" አለኝ።
"a..."
"እየጠበኩህ ነው" አለኝ
"m...."
"ቀጥል ቀጥል " አለኝ። ያቺ ቅልብልቅ መጣችና
"አለቃ ምርመራውን አቁሙት ተበሏል፦ከበላይ" አለች።
"ተባለ እንዴ? ምን ይቀልዳሉ ግን? በቃ ልብሱን አልብሱና ፍቱት" አላቸው። አቋቋሜን አስተካክለው ልብሴን አለበሱና የሱሪየን አቧራ አራገፉልኝ። እጄንም ፈቱልኝ። ኮሌታየን አስተካከሉልኝ። ፀጉሬንም አበስ አበስ አደረጉና አስተካክለው አይኔን የሸፈኑበትን ጨርቅ አነስተው
"Happy Birth Day to you" በለው ቀወጡት። እየተበሳጨሁ ኬክ ቆረስኩ። ወደ ሞት እየተጠጋን እንደሆነ ለሚነግረን እድሜ ሞት ሞት በሸተተ "ሰርፕራይዝ" ተቋጨ። በጥፊ የመታችኝን ማርታን በኬክ ጠፍጥፌ ጣልኳት። "ድንቄም ሰርፕራይዝ!"
ይቺ አስማት የሆነች ሃገር አንኳን ህዝቦቿ አፈሯም እንዲህ ይናፍቃል፡፡ ሃገርክን የካድህ ሁላ አንድ ቀን በናፍቆት አፈሯን ስመህ ሳይሆን በፀፀት ይቀር በይኝ ብለህ እግሯ ስር ትወድቃታለህ፡፡ ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር፡፡

Translate

About Me