Search This Blog

Saturday 14 January 2017

ዘረኝነት የፍቺ ምክንያት ሲሆን
@@@@@@@@@@@
እኔ የምለው በዓሉ እንዴት ነበር? ክርስቶስ ለእኛ ፍቅርን ሊያስተምር የተወለደበትን ቀን እያከበርን ነው። የዘንድሮው የልደት በዓል ከአምናው የሚለየው ዘንድሮ ጥላቻን እየዘሩ ላስቸገሩን አሁንም ፍቅርን እየተማርን የምናስተምርበት መሆኑ ነው። ልበል እንዴ? ለነገሩ አልኩ። ፍቅርን ፍቅር ከሚያውቁ ሁሉ እንማራለን። በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው ሁሉ እንወዳለን። መውደድ ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ ፍቅር፤ ፍቅር ስል ደግሞ ትዳር። እናላችሁ በዚህ በልደት በዓል ረፋድ ላይ ከቤት ወደ ሡቅ ስወጣ ከኋላየ አንድ ወጣት ስልክ እያወራ ይከተለኛል። በዓል እንደመሆኑ ብዙዎቹ ሱቆች ተዘግተው ጎዳናው እረጭ ብሏል። እናም ልጁ የሚያወራው በሙሉ ይሰማኛል። ከንግግሩ ከትዳር ጓደኛው ጋር እንደተለያዩ ተረዳሁ።
"እየውልህ እኔ እኮ ልጅቷን ሳልወዳት ቀርቼ አይደለም። እወዳታለሁ። እንደምትወደኝም አምናለሁ"
ይልና የዚያኛውን ስልክ ደግሞ ይሰማል። ያኛው ከሚስትህ ጋር ታረቁ እያለ እየመከረው እንደሆነ ገባኝ። በዚህ በዓል ከፍቅር እና ከትዳር መለያየት እንዴት እንደሚያስጠላ አስቡት። ግን እንዲህ የሚዋደዱ ከሆነ በምን ምክንያት ሊለያዩ ቻሉ። ልጁ ንግግሩን ቀጠለ።
"ያው የቤቱን እቃ ትቼላት ወጣሁ። ቴሌቭዥን ብትል አልጋ ሁሉንም ትቼላታለሁ እኮ!" እያለ ያወራል። ይሄ ጥል አይባልም ብየ አሰብኩ። ሰውን እየተዋደዱም ቢሆን የሚያለያየው ያ ገንዝብ የሚሉት ሰይጣን ነው ብየ እያሰብኩ እያለ
"እየውልህ እኔ ያ በረሃ የሆነን ቦታ ለእሷ ስል ነበር ተቋቁሜ የኖርኩት። አሁን ግን በቃኝ። ዘረኝነቷ አንገሸገሸኝ" ሲል ጆሮየን ማመን አቃተኝ። ከዚህ በላይ መስማት አልፈለኩም ያለ መንገዴ በቅያሱ ታጥፌ ሸሸሁት። ይሄ የዘረኝነት አባዜ ትዳር ውስጥም መግባቱ አበሳጨኝ። እግዜያብሄር በአምሳሉ የፈጠረውን ፍጡር ሰው መሆኑን ትተን ሰው ያለመሆን አባዜ ሲጠናወተን ራሴን መታኝ። አጥንት መቁጠር እዚህ ድረስ አጥንት ሰብሮ ይገባል። የማል!! ከክርስቶስ ፍቅርን እንማር። መልከም በዓል

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me