Search This Blog

Saturday 14 January 2017

የሩስያ እና የአሜሪካ ፍጥጫ
@@@@@@@@@@@
ምንም እንኳ የእነዚህ የሁለት ጡንቻማ ሃገራት መማዘዝ ቆይቶ እኛን የመሳሰሉ ድሃ ሃገራትን ቢደፈጥጥም ፍጥጫቸው ያጓጓል። አብዛኛው አሜሪካዊ የሩስያ መግነን የሃገራቸውን ሃያልነት ይውጣል ከሚል ፍራቻ ይመስላል ቁጭት ውስጥ ናቸው። በተለይ ደግሞ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ስትጠበቅ የነበረችው ሂላሪ ባልተጠበቀ ሁኔታ በትራምፕ መሸነፏ እና የትራምፕ ማሸነፍ ደግሞ የሩስያ እጅ ነበረበት መባሉ የሩስያን እጀ ረጅምነት እና የአሜሪካንን ዝርክርክነት ያሳየ በመሆኑ ብዙዎችን አበሳጭቷል። ሩስያ የእውነት ይህንን አድርጋ ከሆነ እውነትም ተፅዕኖ እየፈጠረች ነው። ትራምፕ እንደሚሉት እና ሲ አይ ኤ እና የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በሬ ወለደ እያሉ አሜሪካንን እያሳሳቱ ነው የሚሉት ነገር ሚዛን የሚደፋ ከሆነ የሂላሪ አለመመረጥ ሄዶ ሄዶ አሜሪካ ህዝብ ላይ ያርፋል። ምክንያቱም የምርጫ ማሽኑ ካልተጠለፈ እና ትራምፕ በትክክለኛ ምርጫ ከሆነ ያሸነፉት ትራምፕ በቅስቀሳቸው ወቅት የተከተሉት አነጋጋሪ የምርጫ ቅስቀሳዎች አሜሪካውያን ልብ ውስጥ ገብተው ነበር ማለት ነው። ስለዚህ የአሜሪካ ህዝብ በሌሎች ሃገራት ሰዎች በገዛ ሃገራችን በኢኮኖሚ ተበለጥን እና ሌሎችም የሃይማኖት፣የዘር እና የመሳሰሉት ጥላቻዎች ሰርፀው ገብተውበታል ማለት ነው። ያ ደግሞ አሜሪካን ለዘመናት ገነባሁት የምትለው ዲሞክራሲን ገደል የሚከትተው ይመስላል። የሆነው ሆኖ ትራምፕ አሸንፈዋል። ለትራምፕ መመረጥ የሩስያ እጅ መኖሩን ትልቅ መተማመን አለኝ ባለው ሲ አይ ኤ መሰረት የዩ ኤስ ሲናተሮች እንደ ሃገር በሩስያ ላይ እንደ ግለሰብ ደግሞ በፑቲን ላይ ማዕቀብ መጣል አለበት እያሉ ያዙን ልቀቁን እያሉ ነው። ሩስያ በክሬምያ ጉዳይ የተጠለባት ማዕቀብ ሳይነሳ ድጋሚ ሌላ ማዕቀብ የሚጣልባት ከሆነ ካለምንም ጥርጥር መጎዳቷ አይቀርም። መዘዙ ግን ለሌሎችም ይተርፋል።2014ላይ የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ የጣለባት ግዜ ከዚያ አካባቢ የሚመረተውን የግብርና ምርጥ ወደ ሃገር ውስጥ አላስገባም ብላ በርካታ አምራቾችን ለኪሳራ ዳርጋለች። እንደሚታወቀው ሩስያ ከፍተኛ መጠን ያለው የግብርና ምርትን ወደ ሃገሯ ታሰገባለች። በማዕቀቡ ምክንያት አፃፋ ለመመለስ ምርት ማስገባቱን ስታቆም ሳምንት ባለሞላ ግዜ ውስጥ የምዕራቡ ዓለም አምራቾች ተንጫጩ። "እሾኽን በእሾህ" ማለት ይሄ ነው። የአሜሪካንን ጡጫ በዚህ ምድር ላይ ካለ ሩስያ የሚቋቋመው የለም። ለዚህም ነው አሜሪካ ሩስያን የሾርኒ የምትመለከታት። ለማንኛውም ስልጣናቸውን በቅርቡ ለትራምፕ የሚያስረክቡት ኦባማ ሊተላለፍ የሚችለውን ውሳኔ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ውሳኔው ምንም ይሁን ምን "አሜሪካ በምትወስነው ውሳኔ ምላሹን ወደያው ታገኘዋለች" እያሉ ነው የሩስያ ባለስልጣናት። በትራምፕ ማሸነፍ የሚብሰለሰውለው ብዙሃን መገናኛው እና ሲ አይ ኤ ጉዳዩን እያራገበ አሸናፊውን ፕሬዝዳንት አጣብቂኝ ውስጥ ሊከትቱት ነው። ከሩስያ ጋር በጋራ እንሰራለን ያሉት ትራምፕ በሩስያ ላይ ሊወሰድ የታሰበው እርምጃ የተሳሳተ እሳቤ ነው ብለው እየተከራከሩ ቢሆንም ጉዳዩ ገፍቶ ሩስያ ላይ ማዕቀብ ተጥሎ ስልጣናቸውን ከተረከቡ ማጣፊያው ሊያጥራቸው ይችላል። እውነትም በሩስያ እገዛ ከሆነ ወደ ስልጣን የመጡት ደግሞ ይቺን ባለውለታ ሃገር እንዴት አድርገው ያስቀይሟታል? አሜሪካ ከአንጀት ይሁን ከአንገት እንጃ እንጂ በእስራኤል የሰፈራ ፕሮግራም ዙሪያ ከእስራኤል ጋር እስከዚህም የመሆን አዝማሚያ እየታየባት ነው። ወዲያ ደግሞ ቻይና የታይዋይን ጉዳይ በጥንቃቄ ልታየው ይገባል እየተባለች ነው። ስልጣን የሚለቀው የኦባማ አስተዳደር ለትራምፕ ትልቅ የቤት ስራ እያዘጋጁላቸው ነው። ትረምፕ አንድ ግዜ ጡርምባውን ከነፉት "ነፍስ ይማር አሜሪካ" የሚል ድምፅ የሚያወጣ ይመስለኛል።

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me