Search This Blog

Saturday 3 September 2016

መፍትሄው ወይ ከትውልዱ መታረቅ አልያም መታነቅ
@@@@@@@@@@
ወንድ ናቸው!! ሳንፈልግ ጥቅልል አድርገው በብሄር ቋት ውስጥ ሊከቱን ትንሽ ቀራቸው። ሰው ከመሆን ተፈጥሯዊ ፀጋ ሰው ወደ አበጀው ብሄርተኝነት።ሰውነት ሊያከትም፣ እንደ መንጋ ግርርር እያልን የእንስሳዊነት ባህሪ ልንላበስ።ያን ግዜ እንደ ሰው ማሰብ ይቀራል። ሁሉም ለቡድኑ እና ለብሄሩ ብቻ ማሰብ ይጀምራል። ያ ትውልድ ይዞት የመጣው በሽታ። የ ያ ትውልድ አባሎች እናንተ የዚያን ትውልድ አድንቃችሁ አትጠግቡም። ለእኔ ትውልድ ያመጣችሁት አንዳችም ለውጥ ባለመኖሩ እና ይልቁንም በብሄር ቋት ውስጥ ልትከቱን ስለምትለፉ እኛ ስለምን እንውደዳችሁ? አሁን በስልጣን ላይ ያሉትም አብዛኞቹ የ ያ ትውልድ አባል ናቸው። ለዚያም ልንጣጣም አልቻልንም። እናንተ ታግለን የብሄር ብሄረሰቦችን መብት አስከበርን ትሉናላችሁ። እኛ ደግሞ የሰዎችን ወይም የግለሰቦችን መብት መቼ አስከበረችሁ ብለን እንሞግታለን። ቡድን ካለግለሰብ ይፈጠር ይመስል የቡድንን መብት ልትጨፈልቁ ነው የሚል ምላሽ ትሰጡናላችሁ። እናንተ የ ያ ትውልድ አባሎች በሰብዓዊ መብት አያያዝ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ምርጦች ነን ትሉናላችሁ። የእኔ ትውልድ አሁን ይችን እየፃፍኩ ባለበት ቅፅበት ስለ ዓለም ሃገራት የሰብዓዊ መብት አያያዝ የመረጃ መረብን ዘርግቶ ከሌሎች ሃገራት የእንስሳት መብት አያያዝ እንኳ እንደማንሻል ይነግራችኋል። ለምሳሌ
ጃፓን እንስሳትን ስለመቆጣጠር እና ስለመንከባከብ ባወጣችው ህጓ አንቀፅ 2 እንዲህ ይላል።
" All people must not only refrain from killing, injuring, and inflicting cruelty upon animals, but they must also treat animals properly, taking their natural habits into account." ይህንን እናንተ አትነግሩንም። እናንተ በአካል ምናልባትም ለልምድ ልውውጥ በሚል ሃገሩን ታውቁት ይሆናል። እኛ አለም በአንድ መንደር ስር ገብታለች ብለን የፈለግንውን አገር: ቤታችን ሆነን እንጎበኛለን። በጃፓን
ህግ ብቻ ወጥቶ አልቀረም። እንስሳት ላይ ጉዳት ያደረሰም የሚደርስበት ቅጣት ተወስኖ ተግባራዊ እየትተደረገ ነው።
(Penalties)
Article 13. Any person who cruelly treats or who abandons a protected animal shall be liable to a fine or minor fine of not more than thirty thousand yen (~30,000).
እኛ በህግ ደረጃ የምንታማ አይመስለኝም። ያወጣንውን ህግ የማይተገብር ተፈጠረና ህግ አውጪውን ህግ አክብር በሚል ፀብ ላይ ነን። የእኔ ትውልድ ከዚያ ትውልድ ጋር ያልተግባባው በአስተሳሰብ ልዩነት ነው። የ1960ዎቹን አስተሳሰብ ለእኔ ትውልድ ና ተጋት ብትሉት ሌላው ቀርቶ በንግግር እንኳ መግባባት ስለማይቻል ወደ አመፅ ይቀየራል። ችግሩ አመፁን በዚያው ዘመን እሳቤ በዱላ እናበርደዋለን ብላችሁ ታስባላችሁ።
በዚህ ወር ውስጥ በአማራ ክልል በተነሳው ተቃውሞ የሰው ህይወት ጠፍቷል። ከመንግስት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎች ንብረት ጉዳት ደርሶበተል። ይህንን የሰው ህይወት መጥፋት ሰዎች(ከሰውነት ደረጃ የወረዱ እንበል ይሆን?) አንደኛው ወገን የትግራይ ተወላጆች ላይ በዘራቸው ጥቃት ደረሰባችው ብሎ እሪሪ ይላል። ሌላው ወገን ደግሞ አማራው እየተገደለ ነው ይላል። እውነቱ ግን በአካባቢው ሰዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ ነው። ሰው እየተገደለ መሆኑ ነው። ስለምን "በሰዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ይቁም" አላልንም። እዚያ ቦታ ከየትም ይምጣ ከየት ብቻ ሰው ይኖራል።ሰው ከመሆን የተፈጥሮ ፀጋ ወደ ሌላ ሰው ያለመሆን ክሰተት እየተጠፈጠፍን ነው።ከዚህ ካልወጣን እንቸገራለን። አብሮ ተዋልዶ የኖረን ለያይቶ ማቧደን መልሶ ሴራ ጠንሳሹን ነው የሚያጠፋው። እያየንውም ነው።ይቺ ሃገር አስማት ነች።ይሄን ህዝብም በጭራሽ አታውቁትም። አለያየንው ብለን ስንል እድር እና እቁብ ላይ ተሰብስቦ የምናገኘው። ተማርኩ ብሎ ከሚዘባርቀው ሰው እጥፍ የሞራል ልዕልና ያለው ህዝብ። እንኳን ስትሸጠው ስታስማማው የሚያውቅ ህዝብ። የማይሆን ነገር ስትሰራ ተሰልፎ ደግፎ፤ ተሰልፎ መቃብርክን የሚቆፍርልህ። ቢመክርህ ወይም ተው አይሆንም ቢልህ ልታጠቃው እንደምትችል ስለሚያውቅ ለምን ይመክርሃል? ጌታየ ህዝቡን ለማወቅ ጥልቅ የስነ ልቦና ጥናት የሚጠይቅ ነው። እናም ከሰውነት ስትወርድ በርታ እያለ የሚቀብርህ ራሱ ነው። አሁን መፍትሄው ወይ ከትውልዱ መታረቅ አልያም መታነቅ ነው።

Saturday 16 July 2016

Maalan jira
መኪና ስላለህ በእግርህ ወይ በታክሲ አትሄድም አይደል? ትልቅ
ቪላ ቤትህ ውስጥ ብፌ ተዘጋጅቶ ስለምትመገብ አነስ ያሉ
ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች አትገባም አይደል? ግቢህ
ው�ስጥ እሳት አያይዘህ በግ አርደህ በውስኪ ስለምታወራርድ
አነስተኛ መጠጥ ቤቶች እና ጭፈራ ቤቶች አትገባም ይሆናል።
በቃ ተበድለሃል። የሰዎች ፍቅር ተነፍጎሃል። በዚህ ቅንጡ ኑሮህ
ውስጥ በመደበቅህ ወይም ታች ያለ ኑሮ በመናቅህ የሚገርም
ፍቅር አጥተሃል። የማያውቅህ ሰው ፍቅር። የማያውቅህ ሰው
ግፊያ እና ይቅርታ። በዚያውም ትውውቅ። በዚያው ጥልቅ
ወዳጅነት።ቢዚያው ችግሮቻቸውን ማወቅ እና ማየት።እስኪ
በሞቴ ከላይ የነገርኩህን ለአንድ ሳምንት እንኳ አድርገው። ቆይ
እንዲያውም እኔ አነስተኛ ጭፈራ ቤት ይዤህ ልግባማ። ደብረ ብረሃን ነው።ቤቷ
አነስተኛ ናት። ጥቅጥቅ ብላ ሞልታለች። ጥግ ጥግ ባንኮኒ ላይ
ተደግፈው ከሚጠጡት ውጪ ሁሉም ጨርቃቸውን ጥለው
ይጨፍራሉ። ይተቃቀፋሉ። አንዱ ጆሮውን አጎንብሶ ወደ ሌላኛው
ሰው አፍ አስጠግቶ ወሬ ይቀበልና ድጋሚ ያኛው ደግሞ
ጆሮውን ለዚያኛው ሰው ያቀብላል። እልፍ ብሎ የቢራ ጠርሙስ
ይጋጫል። ቺርስስስ! ይቺን አጭር ግዜ በደስታ ለማሳለፍ፤
ያለብንን የህይወት ውጣ ውረድ ለመርሳት፤ ከቤት፣ከሚስት
ወይም ከሌላ ሰው ለመሸሽ፤ ብስቶን ለመተንፈስ ወይ
ለመርሳት፤ብቻ ይጠጣለታል። ጥጉ በሙሉ በመያዙ የቢራየን
አንገት በእጄ አቅፌ ወደ መሃል ገባሁ። ካለ ውዝዋዜ መቆምና
መጠጣት የለም የተባለ ይመስል ቤቷ ወዲያ ወዲህ ትላጋለች።
አንዱ ሙዚቃ አልቆ ሌላው ሙዚቃ ሲገባ የጭፈራ ስልቱ
ተቀይሮ ሌላ ድባብ ይፈጠራል። እዚህ በየ ሰከንዱ ሙዚቃ
ብትቀይር የሚከስስህ የለም። የጭፈራ ስልት ይቀየራል እንጂ።
የሃጫሉ ሁንዴሳ "ማለንጅራ*" ተከፈተ። ያቺ ቤት ተርገበገበች።
ጨፋሪው ትከሻውን እያወዛወዘ መሬቱን በእግሩ እየመታ ቤቷ
እሪሪ ልትል ደረሰች። የዚያ ሁሉ ሰው ትንፋሽ ከመስተዋቱ ላይ
ጤዛ ሰርቶ "ጠብ" ይላል። ሰው ፊቱ ላይ እንደ ጎርፍ
የሚንቆረቆረውን ላብ በጃኬቱ እየጠረገ ያብዳል። በእጄ
የያዝኩትን ቢራ ስጎነጨው ከወትሮው ለየት ብሎ ጣፈጠኝ። ግን
ሞቋል። ያም ቢሆን ይጣፍጣል። ሙዚቃው ሲያልቅ አጣገቤ
ላብበላብ ሆኖ ሲጨፍር የነበረ ወጣት ወደ ጆሮየ ጠጋ ብሎ ደስ
በሚል ቅላፄ
"በናትህ ሙዚቃውን አስደግምልኝ። እኔ ኦሮሞ ነኝ።ዘፈኑን
እወደዋለሁ" አለኝ። ሄጄ ለሙዚቃ አጫዋቹ ሙዚቃውን
እንዲደግምልን ነገርኩት። ሃጫሉ ተደገመ። ልጁ በደስታ
ሰከረ።ድንገት ከአጠገቤ ተሰወረ። ዞር ዞር ስል የለም። ወዲያው
ከጀርባየ ያልተከፈተ ቢራ ታቅፎ መጣ። ጠርሙሳችንን አጋጨን።
አይደክመውም። ሙዚቃው እስከሚያልቅ ጨፈረ። ሌላ ሙዚቃ
ቀጠለ። ጎጃምኛ። ቤቷ አትቆምም። በማንኛውም ሙዚቃ
ይጨፈራል፤ ይጠጣል። በተጀመረው ሙዚቃ እየጨፈረ ያ ልጅ
በድጋሚ "በናትህ የሃጫሉን አስደግምልኝ" አለኝ።
አለመነታሁም። አስደገምኩለት። ለምን ተደገመ አይባልም። ብቻ
ያስጨፍር እንጂ እኔ ራሱ ተነስቼ ብዘፍን የሚቃወም የሚኖር
አይመስለኝም። ምክንያቱም ይህ ጭፈራ ቤት ነውና። ሙዚቃው
ሲጀምር ልጁ የጭፈራ እብደቱ ተነሳበት። እሱ ብቻ አይደለም።
ጭፈራ ቤቱ ውስጥ ያሉ ሁሉ አቧራ የለም እንጂ አቧራውን
አጨሱት። ሙዚቃው ሲያልቅ ወደ ባንኮኒው እየጎተተ ይዞኝ ሄዶ
ፍላጎቴን እንኳ ሳይጠይቀኝ "10 ቢራ ስጠው" ብሎ የ10 ቢራ
ከፍሎ በትከሻው ሰላም ብሎኝ ተጠባብቆ የሚጨፍረውን ሰው
በእጁ እየፈለፈለ ጥሎኝ ወጣ። ምክንያቱም ውስጡን
የሚያይበት ወይም ብሶቱን የሚረዳበትን ነገር አግዠዋለሁና
መሰለኝ!! እናማ ከዚህ በፊት በአይን እንኳ አላውቀውም። እናም
አልኩ። መኪናም ይኑርህ በእግርህም በታክሲም ተንቀሳቀስ።
የፈለገ ድሃ ባትወድ ግዴለም ይሄ ማህበረሰብ የሚውልበት ቦታ
ዋል። ክብሬ ምንትስ አትበል። በስራ ሰዓትህ የፈለገ ትልልቅ
የሃገር ጉዳይ ስታስፈፅም ዋል። ግን በእረፍት ግዜህ ብዙሃኑ
ወደሚውልበት ሂድ። መስሪያ ቤት አብሮህ የሚውል ሰው
ፈርቶህ አልያም የራሱ ጉዳይ ብሎ ስለ አንተ ላይነግርህ
ይችላል እዚህ ግን ሳያውቅ ስላንተ የሚባለውን ሁሉ
ይነግርሃል። ራስህንም ታይበታለህ። ከፈለክም በ6ወር አንዴ
ጥንብዝ ብለህ ስከር!! ብስቶህን ተንፍሰህ ትገላገልበታለህ!!!
ደርግ እንዴት ሊናፍቀን ይችላል? እንዴትም!!
(የመንግስቱን ፎቶ እየለጠፋችሁ ለምታዝጉን ሰዎች ይሁን)
@@@@@@@@@@@@
"....ጠዋት ሚያዝያ 19ቀን 1970 ዓ.ም
በግምት ከንጋቱ 12
ሰዓት ቤታችን ሆነን የተኩስ ድምፅ ሰማን።...በዚያኑ ቀን ወደ
ትምህርት ቤት ስሄድ ወንድሜ ወልደ አብ ደንቡ ተገድሎ
አሥከሬኑ ከቀበሌው ፅ/ቤት ፊትለፊት ካለ አስፓልት መንገድ
ላይ ተጥሎ አይቼ ዝም ብየ በማለፍ ትምህርት ቤት ገባሁ።.....
((ወደ አስከሬኑ(ተጨምቆ)) ከመሄዳችን በፊት በስልፉ ላይ አቶ
ታደሰ መንገሻ፣ ገ/ጊዮርጊስ ስራቱና እንድርያስ ቡታ ሆነው
ስሜን ጠርተው በማውጣት በታጣቂዎች ካስያዙን በኋላ
ለተማሪዎቹ 'የሰባት ቤት ጉራጌ ቀንደኛ መሪ የሆኑት
እነወልደአብ ደንቡ ስለተገደሉ እንኳን ደስ ያላችሁ፣የዛሬውን ቀን
የምናሳልፈው በትምህርት ሳይሆን በሆታና በጭፈራ ነው'
በማለት እኔን እያስመሩ በኋላ ተማሪዎቹ እየተከተሉ ወንድሜ
አስከሬን ዘንድ ደረስን። አስከሬኑን ሳልረግጥ በሁለት እግሬ
መካከል አድርጌ ሳልፍ አቶ እንድርያስ ቡታ ማጅራቴን በመያዝ
በትዕዛዝ አጠራር፣ 'ሰለሞን' በማለት 'ሬሳ እኮ የሚረገጠው
እንዲህ ነው' በማለት በወንድሜ አስከሬን ላይ ቆመበት። ከዚያ
ሳልወድ በግድ የወንድሜን አስከሬን ሆዱ ላይ ረግጬ
አልፊያለሁ።
በሁለት ረድፍ የሚሄዱ የትምህርት ቤቱ ሁለት ሽፍት ቁጥራቸው
በግምት 2,200(የሚደርስ) ተማሪዎች ለገበያ የተገኘው ሰው
ሁሉ አስከሬኑን እንዲረግጥ ተደርጓል።...
"...ገብሬ ሙሄ የተባለው የጉብሬ ት/ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ
የፈጥኝ ታስሮ ከበሬ ጭራ ጋር አስረውት በሬው እየጎተተው ገ/
ጊዮርጊስ ስ�ርአት፣ገረመው እንዳለ፣ ሎባ ኸሊልና ሌሎች
በርካታ ሰዎች በመሆን እየደበደቡት ራሱ ተፈነካክቶ ፈርስ በአፉ
እየወጣ(ስርዝ-ደራሲው) ሲወስዱት አይቻለሁ' ይላል ይህ
ወጣት"...ክፍሉ ታደስ ኢትዮጵያ ሆይ ቅፅ 1 ከገፅ 65 እስከ
66) ይቺ ትንሿ ናት ታዲያ

Friday 17 June 2016

"የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ደጋፊ ስለሆንሽ ቤቴን ልቀቂልኝ" ተባልኩ
@@@@@@@@@@
እኔ የምለው በቃ በልዩነት መኖር አንችልም ማለት ነው? ልዩነት
ውበት ነው የሚባለውስ አባባል ለፖለቲካ አይሰራም ማለት
ነው? የኢህአዴግ ደጋፊዎች የተቃዋሚ ደጋፊዎችን በጣም
ይጠላሉ። የተቃዋሚ ደጋፊዎች ደግሞ የኢህአዴግ ደጋፊዎችን
አምርረው ይጠላሉ። የፖለቲካ አቋም ልዩነት ጥላቻ ላይ ሲደርስ
ማየት ያስጠላል። ማንም ሰው የኢህአዴግ ደጋፊ እንደሆነው
ሁሉ የተቃዋሚ ደጋፊም መሆን መብቱ ነው። በተቃራኒው
የተቃዋሚ ደጋፊ እንደሆነው ሁሉ የመንግስት ደጋፊም መሆን
መብቱ ነው። እርስ በእርስ ግን ጥልቅ ጥላቻ ውስጥ መግባት
ልዩነትን ያለመቀበል ችግር ነው። የእኔን አስተሳብ ይዘህ ኑር፤
እኔ አውቅልሃለሁ የሚል እሳቤ ስለ እውነት ያናድዳል። እርስ
በእርስ ስንወነጃጀል ያለ ለውጥ ሲባሉ መኖር! ወደ ነገሩ
ልግባማ። አንድ ወዳጃችን አከራዮቿ "ቤቱን ልናድሰው ነው"
ብለዋት ቤት እንደምትፈልግ ስትነግረን ወራት አልፈው ነበር።
በመካከል ቤቱን እየፈለግንላት ብናይም ብናይም ቤቱ
አይታደስ። "ቤት አገኘሽ?" ትላታለች አከራዮዋ።
"ቆይ ገና ነኝ።እድሳት እስክትጀምሩ ማግኘቴ አይቀርም"
ትላቸዋለች። እስኪታደስ ድረስ ዝም ብላ መኖሯ ነው ብላ ነው
መስለኝ ትላንት አከራዩዋ እንቅጩን ነገረቻት።"ቤቱን ልናድሰው
ነው ያልንሽ ውሸታችንን ነው። ጋዜጠኛ እና የኢህአዴግ ደጋፊ
ስለሆንሽ እናንተን ማከራየት ስለማንፈግ እንድትለቂ ነው"
አለቻት። በጣም ያዘንኩት በጥላቻ ለተሞላው ፖለቲካችን ነው።
ሲጀመር እነሱ መንግስትን እንደሚቃወሙት ሁሉ እሷም
መንግስትን የመደገፍ መብት አላት። ብቻ በነገሮች አዘንኩ።
ሳስበው ግን እንዲህ ያለ አሰተሳሰብ እንዲመጣ ያደረጉት
ራሳቸው የኢህአዴግ ደጋፊዎች ናቸው። 97 ላይ የቅንጅትን
ደጋፊ ለምን ቤት አከራያችሁ ተብለው የተወቀሱ አከራዮች
እንዳሉ አውቃለሁ። ይሄው ነገሩ ተገለበጠ እና እርፍፍ።

Wednesday 8 June 2016

የፍርሃት ቆፈን

የፍርሃት ቆፈን በተመስገን እህት አዕምሮ ውስጥ
@@@@@@
ያቺን የቡና ሱሴን ለማሟላት ከሰፋራችን ካለች ምግብ ቤት ጎራ
አልኩ። ቤቷ ትንሽየ ብትሆንም ቡና፣ የአልኮል መጠጥ እና
ምግብም ይሸጥባታል። ከሰል ምድጃው ላይ የተጣደውን ጀበና
አይን አይኑን ሳይ የሆኑ ጥቁር ወፍራም ሴትዮ መጡና ከፊት
ለፊቴ ቢራ ከሚጠጡት ወንዶች ጋር ተቀላቀሉ። ወዲያው ነው
ቢራ የተሰጣቸው። ወንዶቹ በአካባቢ ይነቋቆራሉ። ጎጃሜ እና
ጉራጌ በንግድ ፣ ጎንደሬ በሰሊጥ፣ ሸዋ.... ምናምን እያሉ
ይሽካካሉ። ሴትዮዋ ሲገቡ ትንሽ ተሳሳቁና ነገሩን ወደ ጭቅጭቅ
ቀየሩት። 3ቱም ወንዶች ሴትዮዋን በነገር ያዋክቧቸው ጀመር።
አንዱ፦ "በምን እናውቀለን የእሱ እህት መሆንሽን? ሰው ታዋቂ
ሰው እየፈለገ እህቴ ነው፣ ወንድሜ ነው ፣የአጎቴ ልጅ ነው
፣ምናምን እያለ ሆዳችንን ይነፋዋል።"
ሴትዮዋ፦" እሱም እንደ እኔ ጎራዳ ባሪያ ነው።"
ሌላኛው፦ "አናምንሽም ባክሽ።"
ሴትዮዋ በጣም እየተበሳጩ መጡ።
አንደኛው፦ ወንድምሽ ተው አትፃፍ ይቅርብህ ሲባል ነው ከርቸሌ
የተወረወረው ።አልሰማ ብሎ። ደግሞ ምን ጎደለበትና ነው
መንግስትን የሚቃወመው? ድልድይ ተሰራ፣ መንገድ ተሰራ ፣
ይሄው አሁን ደግሞ አባይ ሊገደብ ነው። ምን ልሁን ብሎ ነው?
" አላቸው።ከት ብሎ ይስቃል።
ሴትዮዋ ገልመጥ ገልመጥ ማለት ጀመሩ።
ያኛው፦ ተናገሪ እንጂ ምን ያስፈራሻል?
ሴትዮዋ፦ የእኔ ወንድም ነግሯቸዋል። እኔ ሌባ አይደለሁም።
በፊት ግን አዎ ቸግሮኝ እሰርቅ ነበር ብሏቸዋል። ብለው
ያልተወራ ቀላቀሉበት። ከጎናቸው ላለው ወጣት የሆነ ነገር ሹክ
አሉት።
ሰውየው፦ "አይዞሽ ማንም አትፍሪ። ማንም አይናገርብሽም። ቆይ
ግን ትፈሪያለሽ እንዴ? " አላቸው
ሴትዮዋ ፦ "እንዴት አልፈራም?"ብለው መለሱ።
-ይህን ግዜ እሱ ቢሆን ከየትም ከየትም ብሎ ምላሽ አያጣም
ነበር"ብሎ ወደ ውጭ ወጣ።ከጎኔ ያለው ሰውየ ወደ ጆሮየ ጠጋ
ብሎ
- ተመስገንን ታውቀዋለህ?" አለኝ
- ተመስገን የቱ? ብየ ጥያቄውን በጥያቄ መለስኩለት።
-ተመስገን ደሳለኝ ጋዜጣ ላይ ይፅፍ የነበረው።"
- አዎ አውቀዋለሁ።
- "የእሱ እህት ናት። የታሰረ ሰሞን እስር ቤት ሄዳ ገርፈውት
አይታው እንደዚህ ንክ ሆና ቀረች" አለኝ።አሁን የፈለጋትን ነው
የምትናገረው ግን ስትፈራ አይጣል" አለኝ።ሴትዮዋን አየኋቸው
ድጋሚ ቢራ አዘዙ።
"በጥይት ቢመቱት እዳው ብዙ ነው፤
በለው በእስኪብርቶ ሰንበር በሌለው።" የሚለውን ግጥም
ገልብጨ ገጠምኩት።

Sunday 5 June 2016

08 08 08 08:08 ማላ እና ሞቴን አገጣጠመዉ



08 08 08 08:08 ገንዘብ ስላልሰጣችሁኝ ስማችሁን ለማጥፋት የፈጠርኳት ሰዓትና ቀን ናት
     (አዲስ መኮንን)


አንዱ ወዳጄ 5ኛ ፎቅ ከሚገኘዉ ቢሯችን መጣና ዩኒቨርሰቲዉ የኪነጥበብ ሰዎችን የትም በተናቸው እኮ  አለኝ፡፡
"የቱ ዩኒቨርሲቲ" ብየ ጠየኩት
"ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ነዋ" አለኝ። የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ከጠረጴዛየ ላይ እየወረወረልኝ። አነበብኩት።  የፊደል ገበታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የፍኖተ ንባብ አዘጋጆች የፍቅር እስከ መቃብርን 50 ዓመት በዓል ለማክበር አርቲስቶችን ሰብስበው ወደ ጎጃም ተጉዘዋል። "ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሊቀበለን ቃል ገብቶ የትም በተነን" የሚል ወቀሳ ነው። እንዴት ሊሆን ቻለ ብየ ትንሽ አንሰላሰልኩ። ከመፍረዴ በፊት ማረጋገጥ ነበረብኝ። ወዲያው አንዱ ከሚኒሚዲያ ያልዘለለ ጣቢያ ላይ ጉዳዩ እንደተወራ ሰማሁ። ለዚየውም 12 ደቂቃ ያክል አውርተውበታል አሉኝ። በጣቢያው እምነት ባይኖረኝም አዲስ ዘመንን ለማመን ተገደድኩ። የሆነ ስህተት ተፈጥሮ ችግሩ አጋጥሟል ብየ ደመደምኩ።
    ግንቦት 27 እና 28 የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ባዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ እንድሳተፍ ተጋበዝኩ። በአስገራሚው አውደ ጥናት ላይ በመጋበዜ መደሰቴን ገልጬ ለጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለዶክተር ስማቸው ጥይቄውን አቀርብኩላቸው። "እንዴት ቃላችሁን አጥፋችሁ ልዑካን ቡድኑን አንቀበላችሁም አላችሁ" አልኳቸው። ዶክተሩ ፈገግ ብለው መለሱልኝ። በፈገግታቸው ውስጥ አንዳች ንዴት ይተናነቃቸዋል።" ስፖንሰር እንድናደርጋቸው ደብደቤ ፅፈውልን መልስ ስላልሰጣናቸው ነው። ሲጀመር እኛ የባህል ማዕከሉ ትልቅ አውደ ጥናት ስላለው አንድ ጋር እንስራ ብለናቸው ነበር" አሉኝ። ዶክተሩ በስም ማጥፋቱ መናደዳቸው እያሰበቀባቸው ሄደ። "እንዲያውም እስኪ እሺ ያላቸው አካል ካለ ይምጡ" አሉኝ።
    የራሴን የማጣራት ስራ መስራት ነበረብኝ። የአዲስ ዘመንን ድህረ ገፅ ጎበኘሁ። አነበብኩት። ዩኒቨርሲቲውን ስፖንሰር ጠያቂው የፍኖተ ንባብ ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ አቶ አንተነህ ከበደ ነው። ፅሁፉን የፃፈው ደግሞ ዋለልኝ አየለ ነው። እኔ ግን በዋለልኝ ስም እንዲታተም ተደረገ እንጂ ሴራዋ የአንተነህ ነች። ምክንያቱ ደግሞ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሃዲስ አለማየሁ የተሰየመ የባህል ጥናት ተቋም ስላለው በሃዲስ አለማየሁ ስም ብንሄድ እና ገንዘብ ብንጠይቅ አናጣም ብሎ ተነስቶ ሳይሳካ በመቅረቱ ነው።
        ፅሁፉን እያጣቀስን እንመልከት። " ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሲመሠረት ሀዲስ አለማየሁንም ለመዘከር ተብሎ እንደነበር ዩኒቨርሲቲው ቢዘነጋውም ብዙ ሰዎች ያስታውሱታል ብዬ አምናለሁ።" ይላል። የትኛውም ዩኒቨርሲቲ ሲመሰረት ሶስት ዓላማዎችን ማለትም መማር ማስተማር፣ጥናትና ምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሉትን ይዞ እንጂ ግለሰብን ወይም ድርጅትን ለመዘከር ተብሎ ወይም ሁለተኛ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ የለም። ፅሁፉ ሳተ። በርዕሱ ላይ 08 08 08 08:08 ላይ ነው ነገሩ ገጠመብን ያሉት። 07:50 ደጀን ደረስን ካሉ 8:08 እንዴትም ማርቆስ አይድርሱም። ቢበዛ ሉማሜ ይደርሱ እንደሆን እንጂ።(ምናለ ድምር ላይ እንኳ ጥሩ ማጭበርበር ቢያደርጉ) እና እንዴት ሆኖ ነው ዩኒቨርሲቲው ሃዲስ አለማየሁ ምኔም አይደሉ ብሎ ፕሮግራሙን ሰረዘብን ብለው ሊሉ የቻሉት። በዚህ ደቂቃ እንዴት አወቁ? ደጀን ደረሰናልና ተቀበሉን ብለው ስልክ ደውለው? ወይስ ለወሬው ድምቀት የተፈለሰፈች ቀመር? እውነቱን እናውራ ከተባለ ለወሬ ማድመቂያ የተፈጠረች ትመስላለች።
    ሌላው አንድም የዩኒቨርስቲውን አመራር ጠቅሰው ሊነግሩን አልፈለጉም።እከሌ እንዲህ ብሎናል አላሉም። ለምን? የጋዜጠኝነት ሙያስ በእውር ድንብር የሚመራ ነው? አንድ ፅሁፍ ባለቤት ይኖረዋል። እነ አንተነህ የጥቅም ግጭት የጋዜጠኝነቱን ሙያ አሳታቸው እንበል። አዲስ ዘመን እንደ ሙያ ፅሁፉን ባላንስ አልተደረገም። ስለምን አልተደረገም? አዲስ ዘመን ለምንስ እንደ ጋማ ከብት ሳያመነዥክ አተመው።
       በመጨረሻ ስለምን ዩኒቨርሲቲው ግቢ ደርሰው አንድ ሰው እንኳ ለማናገር አልሞከሩም? አንድን ትልቅ ተቋም ያለምንም ማስረጃ ስም ማጥፋት ወንጀል ነው? በአሁኑ አውደ ጥናት ላይ ስሳተፍ ብዙ ነገሮችን አይቻለሁ። ሌላው ቀርቶ ለአርቲስት ዮሃንስ አፍወርቅ (ፍቅር እስከመቃብር ላይ ዋሽንት አናጋሪው) 160 ብር አውጥቶ ቪሲዲ አዘጋጅቶ ሸጠዉጠቀሙ ብሎ የሰጠ ተቋም ነው። ስለ ሃዲስ አለማየሁም 4 በላይ ጥናታዊ ፅሆፎችን በአንድ አውደ ጥናት ያስኬደ ተቋም ነው። እንዲያዉም ከሀዲስ አለማየሁ ዉጭ ሌሎች አይዘከሩም ወይ የተባለ ነዉ፡፡
        እነ አንተነህ እንደሚሉት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሀዲስ አለማየሁ ጉዳይ « ለእኔ ምኔም አይደለም» ቢል ኖሮ በስማቸው የባህል ማዕከል አይከፍትም ነበር፤ ሃውልት አያሰራም ነበር፤ ይህንን ያክል አውደ ጥናትም አያዘጋጅ ነበር። ገና ለገና የሚዲያውን እድል አገኘሁ ተብሎ የጋዜጠኝነትን ሙያ መጣስ አስነዋሪ ነው። አዲስ ዘመንም እንዲሁ።

Translate

About Me