Search This Blog

Friday 17 June 2016

"የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ደጋፊ ስለሆንሽ ቤቴን ልቀቂልኝ" ተባልኩ
@@@@@@@@@@
እኔ የምለው በቃ በልዩነት መኖር አንችልም ማለት ነው? ልዩነት
ውበት ነው የሚባለውስ አባባል ለፖለቲካ አይሰራም ማለት
ነው? የኢህአዴግ ደጋፊዎች የተቃዋሚ ደጋፊዎችን በጣም
ይጠላሉ። የተቃዋሚ ደጋፊዎች ደግሞ የኢህአዴግ ደጋፊዎችን
አምርረው ይጠላሉ። የፖለቲካ አቋም ልዩነት ጥላቻ ላይ ሲደርስ
ማየት ያስጠላል። ማንም ሰው የኢህአዴግ ደጋፊ እንደሆነው
ሁሉ የተቃዋሚ ደጋፊም መሆን መብቱ ነው። በተቃራኒው
የተቃዋሚ ደጋፊ እንደሆነው ሁሉ የመንግስት ደጋፊም መሆን
መብቱ ነው። እርስ በእርስ ግን ጥልቅ ጥላቻ ውስጥ መግባት
ልዩነትን ያለመቀበል ችግር ነው። የእኔን አስተሳብ ይዘህ ኑር፤
እኔ አውቅልሃለሁ የሚል እሳቤ ስለ እውነት ያናድዳል። እርስ
በእርስ ስንወነጃጀል ያለ ለውጥ ሲባሉ መኖር! ወደ ነገሩ
ልግባማ። አንድ ወዳጃችን አከራዮቿ "ቤቱን ልናድሰው ነው"
ብለዋት ቤት እንደምትፈልግ ስትነግረን ወራት አልፈው ነበር።
በመካከል ቤቱን እየፈለግንላት ብናይም ብናይም ቤቱ
አይታደስ። "ቤት አገኘሽ?" ትላታለች አከራዮዋ።
"ቆይ ገና ነኝ።እድሳት እስክትጀምሩ ማግኘቴ አይቀርም"
ትላቸዋለች። እስኪታደስ ድረስ ዝም ብላ መኖሯ ነው ብላ ነው
መስለኝ ትላንት አከራዩዋ እንቅጩን ነገረቻት።"ቤቱን ልናድሰው
ነው ያልንሽ ውሸታችንን ነው። ጋዜጠኛ እና የኢህአዴግ ደጋፊ
ስለሆንሽ እናንተን ማከራየት ስለማንፈግ እንድትለቂ ነው"
አለቻት። በጣም ያዘንኩት በጥላቻ ለተሞላው ፖለቲካችን ነው።
ሲጀመር እነሱ መንግስትን እንደሚቃወሙት ሁሉ እሷም
መንግስትን የመደገፍ መብት አላት። ብቻ በነገሮች አዘንኩ።
ሳስበው ግን እንዲህ ያለ አሰተሳሰብ እንዲመጣ ያደረጉት
ራሳቸው የኢህአዴግ ደጋፊዎች ናቸው። 97 ላይ የቅንጅትን
ደጋፊ ለምን ቤት አከራያችሁ ተብለው የተወቀሱ አከራዮች
እንዳሉ አውቃለሁ። ይሄው ነገሩ ተገለበጠ እና እርፍፍ።

Wednesday 8 June 2016

የፍርሃት ቆፈን

የፍርሃት ቆፈን በተመስገን እህት አዕምሮ ውስጥ
@@@@@@
ያቺን የቡና ሱሴን ለማሟላት ከሰፋራችን ካለች ምግብ ቤት ጎራ
አልኩ። ቤቷ ትንሽየ ብትሆንም ቡና፣ የአልኮል መጠጥ እና
ምግብም ይሸጥባታል። ከሰል ምድጃው ላይ የተጣደውን ጀበና
አይን አይኑን ሳይ የሆኑ ጥቁር ወፍራም ሴትዮ መጡና ከፊት
ለፊቴ ቢራ ከሚጠጡት ወንዶች ጋር ተቀላቀሉ። ወዲያው ነው
ቢራ የተሰጣቸው። ወንዶቹ በአካባቢ ይነቋቆራሉ። ጎጃሜ እና
ጉራጌ በንግድ ፣ ጎንደሬ በሰሊጥ፣ ሸዋ.... ምናምን እያሉ
ይሽካካሉ። ሴትዮዋ ሲገቡ ትንሽ ተሳሳቁና ነገሩን ወደ ጭቅጭቅ
ቀየሩት። 3ቱም ወንዶች ሴትዮዋን በነገር ያዋክቧቸው ጀመር።
አንዱ፦ "በምን እናውቀለን የእሱ እህት መሆንሽን? ሰው ታዋቂ
ሰው እየፈለገ እህቴ ነው፣ ወንድሜ ነው ፣የአጎቴ ልጅ ነው
፣ምናምን እያለ ሆዳችንን ይነፋዋል።"
ሴትዮዋ፦" እሱም እንደ እኔ ጎራዳ ባሪያ ነው።"
ሌላኛው፦ "አናምንሽም ባክሽ።"
ሴትዮዋ በጣም እየተበሳጩ መጡ።
አንደኛው፦ ወንድምሽ ተው አትፃፍ ይቅርብህ ሲባል ነው ከርቸሌ
የተወረወረው ።አልሰማ ብሎ። ደግሞ ምን ጎደለበትና ነው
መንግስትን የሚቃወመው? ድልድይ ተሰራ፣ መንገድ ተሰራ ፣
ይሄው አሁን ደግሞ አባይ ሊገደብ ነው። ምን ልሁን ብሎ ነው?
" አላቸው።ከት ብሎ ይስቃል።
ሴትዮዋ ገልመጥ ገልመጥ ማለት ጀመሩ።
ያኛው፦ ተናገሪ እንጂ ምን ያስፈራሻል?
ሴትዮዋ፦ የእኔ ወንድም ነግሯቸዋል። እኔ ሌባ አይደለሁም።
በፊት ግን አዎ ቸግሮኝ እሰርቅ ነበር ብሏቸዋል። ብለው
ያልተወራ ቀላቀሉበት። ከጎናቸው ላለው ወጣት የሆነ ነገር ሹክ
አሉት።
ሰውየው፦ "አይዞሽ ማንም አትፍሪ። ማንም አይናገርብሽም። ቆይ
ግን ትፈሪያለሽ እንዴ? " አላቸው
ሴትዮዋ ፦ "እንዴት አልፈራም?"ብለው መለሱ።
-ይህን ግዜ እሱ ቢሆን ከየትም ከየትም ብሎ ምላሽ አያጣም
ነበር"ብሎ ወደ ውጭ ወጣ።ከጎኔ ያለው ሰውየ ወደ ጆሮየ ጠጋ
ብሎ
- ተመስገንን ታውቀዋለህ?" አለኝ
- ተመስገን የቱ? ብየ ጥያቄውን በጥያቄ መለስኩለት።
-ተመስገን ደሳለኝ ጋዜጣ ላይ ይፅፍ የነበረው።"
- አዎ አውቀዋለሁ።
- "የእሱ እህት ናት። የታሰረ ሰሞን እስር ቤት ሄዳ ገርፈውት
አይታው እንደዚህ ንክ ሆና ቀረች" አለኝ።አሁን የፈለጋትን ነው
የምትናገረው ግን ስትፈራ አይጣል" አለኝ።ሴትዮዋን አየኋቸው
ድጋሚ ቢራ አዘዙ።
"በጥይት ቢመቱት እዳው ብዙ ነው፤
በለው በእስኪብርቶ ሰንበር በሌለው።" የሚለውን ግጥም
ገልብጨ ገጠምኩት።

Sunday 5 June 2016

08 08 08 08:08 ማላ እና ሞቴን አገጣጠመዉ



08 08 08 08:08 ገንዘብ ስላልሰጣችሁኝ ስማችሁን ለማጥፋት የፈጠርኳት ሰዓትና ቀን ናት
     (አዲስ መኮንን)


አንዱ ወዳጄ 5ኛ ፎቅ ከሚገኘዉ ቢሯችን መጣና ዩኒቨርሰቲዉ የኪነጥበብ ሰዎችን የትም በተናቸው እኮ  አለኝ፡፡
"የቱ ዩኒቨርሲቲ" ብየ ጠየኩት
"ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ነዋ" አለኝ። የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ከጠረጴዛየ ላይ እየወረወረልኝ። አነበብኩት።  የፊደል ገበታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የፍኖተ ንባብ አዘጋጆች የፍቅር እስከ መቃብርን 50 ዓመት በዓል ለማክበር አርቲስቶችን ሰብስበው ወደ ጎጃም ተጉዘዋል። "ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሊቀበለን ቃል ገብቶ የትም በተነን" የሚል ወቀሳ ነው። እንዴት ሊሆን ቻለ ብየ ትንሽ አንሰላሰልኩ። ከመፍረዴ በፊት ማረጋገጥ ነበረብኝ። ወዲያው አንዱ ከሚኒሚዲያ ያልዘለለ ጣቢያ ላይ ጉዳዩ እንደተወራ ሰማሁ። ለዚየውም 12 ደቂቃ ያክል አውርተውበታል አሉኝ። በጣቢያው እምነት ባይኖረኝም አዲስ ዘመንን ለማመን ተገደድኩ። የሆነ ስህተት ተፈጥሮ ችግሩ አጋጥሟል ብየ ደመደምኩ።
    ግንቦት 27 እና 28 የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ባዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ እንድሳተፍ ተጋበዝኩ። በአስገራሚው አውደ ጥናት ላይ በመጋበዜ መደሰቴን ገልጬ ለጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለዶክተር ስማቸው ጥይቄውን አቀርብኩላቸው። "እንዴት ቃላችሁን አጥፋችሁ ልዑካን ቡድኑን አንቀበላችሁም አላችሁ" አልኳቸው። ዶክተሩ ፈገግ ብለው መለሱልኝ። በፈገግታቸው ውስጥ አንዳች ንዴት ይተናነቃቸዋል።" ስፖንሰር እንድናደርጋቸው ደብደቤ ፅፈውልን መልስ ስላልሰጣናቸው ነው። ሲጀመር እኛ የባህል ማዕከሉ ትልቅ አውደ ጥናት ስላለው አንድ ጋር እንስራ ብለናቸው ነበር" አሉኝ። ዶክተሩ በስም ማጥፋቱ መናደዳቸው እያሰበቀባቸው ሄደ። "እንዲያውም እስኪ እሺ ያላቸው አካል ካለ ይምጡ" አሉኝ።
    የራሴን የማጣራት ስራ መስራት ነበረብኝ። የአዲስ ዘመንን ድህረ ገፅ ጎበኘሁ። አነበብኩት። ዩኒቨርሲቲውን ስፖንሰር ጠያቂው የፍኖተ ንባብ ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ አቶ አንተነህ ከበደ ነው። ፅሁፉን የፃፈው ደግሞ ዋለልኝ አየለ ነው። እኔ ግን በዋለልኝ ስም እንዲታተም ተደረገ እንጂ ሴራዋ የአንተነህ ነች። ምክንያቱ ደግሞ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሃዲስ አለማየሁ የተሰየመ የባህል ጥናት ተቋም ስላለው በሃዲስ አለማየሁ ስም ብንሄድ እና ገንዘብ ብንጠይቅ አናጣም ብሎ ተነስቶ ሳይሳካ በመቅረቱ ነው።
        ፅሁፉን እያጣቀስን እንመልከት። " ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሲመሠረት ሀዲስ አለማየሁንም ለመዘከር ተብሎ እንደነበር ዩኒቨርሲቲው ቢዘነጋውም ብዙ ሰዎች ያስታውሱታል ብዬ አምናለሁ።" ይላል። የትኛውም ዩኒቨርሲቲ ሲመሰረት ሶስት ዓላማዎችን ማለትም መማር ማስተማር፣ጥናትና ምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሉትን ይዞ እንጂ ግለሰብን ወይም ድርጅትን ለመዘከር ተብሎ ወይም ሁለተኛ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ የለም። ፅሁፉ ሳተ። በርዕሱ ላይ 08 08 08 08:08 ላይ ነው ነገሩ ገጠመብን ያሉት። 07:50 ደጀን ደረስን ካሉ 8:08 እንዴትም ማርቆስ አይድርሱም። ቢበዛ ሉማሜ ይደርሱ እንደሆን እንጂ።(ምናለ ድምር ላይ እንኳ ጥሩ ማጭበርበር ቢያደርጉ) እና እንዴት ሆኖ ነው ዩኒቨርሲቲው ሃዲስ አለማየሁ ምኔም አይደሉ ብሎ ፕሮግራሙን ሰረዘብን ብለው ሊሉ የቻሉት። በዚህ ደቂቃ እንዴት አወቁ? ደጀን ደረሰናልና ተቀበሉን ብለው ስልክ ደውለው? ወይስ ለወሬው ድምቀት የተፈለሰፈች ቀመር? እውነቱን እናውራ ከተባለ ለወሬ ማድመቂያ የተፈጠረች ትመስላለች።
    ሌላው አንድም የዩኒቨርስቲውን አመራር ጠቅሰው ሊነግሩን አልፈለጉም።እከሌ እንዲህ ብሎናል አላሉም። ለምን? የጋዜጠኝነት ሙያስ በእውር ድንብር የሚመራ ነው? አንድ ፅሁፍ ባለቤት ይኖረዋል። እነ አንተነህ የጥቅም ግጭት የጋዜጠኝነቱን ሙያ አሳታቸው እንበል። አዲስ ዘመን እንደ ሙያ ፅሁፉን ባላንስ አልተደረገም። ስለምን አልተደረገም? አዲስ ዘመን ለምንስ እንደ ጋማ ከብት ሳያመነዥክ አተመው።
       በመጨረሻ ስለምን ዩኒቨርሲቲው ግቢ ደርሰው አንድ ሰው እንኳ ለማናገር አልሞከሩም? አንድን ትልቅ ተቋም ያለምንም ማስረጃ ስም ማጥፋት ወንጀል ነው? በአሁኑ አውደ ጥናት ላይ ስሳተፍ ብዙ ነገሮችን አይቻለሁ። ሌላው ቀርቶ ለአርቲስት ዮሃንስ አፍወርቅ (ፍቅር እስከመቃብር ላይ ዋሽንት አናጋሪው) 160 ብር አውጥቶ ቪሲዲ አዘጋጅቶ ሸጠዉጠቀሙ ብሎ የሰጠ ተቋም ነው። ስለ ሃዲስ አለማየሁም 4 በላይ ጥናታዊ ፅሆፎችን በአንድ አውደ ጥናት ያስኬደ ተቋም ነው። እንዲያዉም ከሀዲስ አለማየሁ ዉጭ ሌሎች አይዘከሩም ወይ የተባለ ነዉ፡፡
        እነ አንተነህ እንደሚሉት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሀዲስ አለማየሁ ጉዳይ « ለእኔ ምኔም አይደለም» ቢል ኖሮ በስማቸው የባህል ማዕከል አይከፍትም ነበር፤ ሃውልት አያሰራም ነበር፤ ይህንን ያክል አውደ ጥናትም አያዘጋጅ ነበር። ገና ለገና የሚዲያውን እድል አገኘሁ ተብሎ የጋዜጠኝነትን ሙያ መጣስ አስነዋሪ ነው። አዲስ ዘመንም እንዲሁ።

Translate

About Me