Search This Blog

Thursday 2 June 2016

እኛ የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች

ዳንኤል ክብረት ”እኛ እኮ በቶም እና ጄሪ ፊልም ያደግን፤ በመንገድ ላይ የተጫወትን፤ በሬዲዮ ካሴት ሙዚቃ ያዳመጥን፤ የመጨረሻዎቹ ትዉልዶች ነን’’ የሚል ፅሁፍን መነሻ አድርጎ ‘’እኛ የ1940ዎቹ ፤50ዎቹ እና 60ዎቹ የኢትዮጵያ ትዉልዶች ….’’ ብሎ አንድ ፅሁፍ ፅፏል፡፡ ምንም እንኩዋ እንዳንድ የ1990ዎቹን ክስተቶች አስገብቶ ቢደነቅርም፡፡
አስኪ እኔም የኖርኩባትን ከ1980ዎቹ ወዲህ ያሉትን ተንተርሼ ትንሽ ልበል፡፡ እዉነትም የዳንኤል ክብረት ትዉልዶች የመጨረሻዎቹ እኛ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
እኛ የ1980ዎቹ፤የ1990ዎቹ እና የ2000ዎቹ ትዉልዶች ጣልያን የሰራዉን መንገድ አፍርሰን ቻይና በሰራዉ መንገድ ላይ የተጓዝን ፤ድልድዩን ንቀን የህዳሴዉን ድልድይ አሰርተን የፎከርን፤በላዩ ላይ የሄድን ፤ አባይን እንገድባለን ብለን የፎከርን፤ተማሪ ሆነንም ተመርቀን ወጥተንም ለግድቡ ማሰሪያ ብር ያዋጣን ፤ ዩኒቨርስቲ ሆነን አንድ ወር ስጋ ትተን ለግድቡ የለገስን ፤ትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆች እንደ አሸን ሲበረክቱ ያየን ፤ ዩኒቨርሲቲዎች በቁጥር 30 ቤት ዉሰጥ ሲገቡ ያየን፤የተማረ ሰዉ ተብሎ ዲግሪ እና ዲፕሎማ ይዞ ድንጋይ ሲጠርብ ያየን ፤ አብረንም የጠረብን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
የፖለቲካ ፓረቲዎችን የምረጡኝ ቅስቀሳ በሬዲዮ የሰማን በቴሌቭዥን ያየን፤በፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክት የተነቁዋቆርን በመንግስትም በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተሰለፍን ፤ሰብል ስብሰባ ተብለን የአንድ ቀን ተምህርት ዘግተን ሰብል የሰበሰብን፤የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሬት ላራሹ ሳይሆን ምግብ ተበላሸ በማለት እረብሻ ሲያስነሱ ያየን እና የተሳተፍን ፤መንገድ ላይ ከተገኘዉ ሰዉ ጋር ታፍስን የታሰርን ፤በጥቁር ጎማ የተገረፍን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
ሚሊኒየም የሚባል ትልቅ ምእራፍ የተሻገርን፤ሚሊኒየም ሚሊኒየም ሲባል መንፈሳችን የሸፈተ፤’’በሚሊኒየም ምን አስባችኋል?’’ ስንባል ኢትዮጵያን ካደጉት አገሮች ተርታ ማሰለፍ ብለን በደንፎ የፎከርን፤ ቤተሰቦቻንን፣ መምህራኖቻችንን እዲሁም ፖሊሶችን በአራዳ ቋንቋ የሸወድን፤
ነጋዴዎች ጨዉ ሊጠፋ ነው እያሉ በ50 ብር ሲሸጡ ያየን፤ ከዚህ በላይ ሳይወደድ እንግዛ ብለን ተሯሩጠን የገዛን፤ ነጋዴዎች ሲያዙ፣ሲታሰሩ፣ሱቃቸዉ ሲዘጋ፣ ያየን፤ ስኳር ከቀበሌ የገዛን የመጀመሪያዎቹ ትውልዶች ነን፡፡
መሪ ሲሞት ያየን፤ ሲቀበር ያለቀስን፤ ለለቅሶ አይተንው የማናዉቀዉን ቤተ መንግስት ያየን፤ ለአንድ ሳምንት በቴሌቭዥን ለቅሶ ያየን፤ ያለቀስን ፤የስልጣን ሽግሽግ ሲደረግ ለመታዘብ የቻልን፤ ትምክተኛ፣ ጠባብ ፣ብሄርተኛ፣ ህገ-መንግስት ናጅ ፣ፀረ ዲሞክራሲ ፣ተግዳሮት፣ የሚሉት ቃላት ሲፈጠሩ የሰማን፤ አብረን ያልን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
ዘመናዊነትን ያየን፤ በኮምፒዉተር የተማርን፤ በሞባይል፣ በአይፓድ፣ በዲቨዲ፣ ሙዚቃ የሰማን፤ በሞባይል ኢነተርኔት የተጠቀምን፤ ፌስ ቡክ በሚባል ማህበራዊ ድህረገፅ ጓደኛ ያፈራን፤ የተጀናጀንን፤ ቺክ የጠበስን(ይህ ንግግር የእነ ዳንኤል ትዉልዶች አይገባቸዉ ይሆን እነዴ?) ሲጋቡ ያየን፤ ዉጭ ካሉ ጓደኞቻችን ጋር በስካይፒ ያወራን፤ ፎቶ ተነስተን በአዶቤ አቀናብረን ቆንጆ አድርገን ፌስ ቡክ ላይ ለጥፈን ያሳየን፤ ቻት ያደረግን፤ በጎግል የቡድን ስራ የሰራን ፤ፈተና በሞባይል ሜሴጅ የተኮራረጅን፤ ይሄ ሲታወቅብን በኤር ፎን የተኮራረጅን፤ የክፍል ለክፍል ዉድደር በምልክት ተኮራርጀን ያሸነፍን፤ የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
ሃይሌ ገ/ስላሴን፣ ቀነኒሳ በቀልን፣ ጥሩነሽ ዲባባን፣ መሰረት ደፋርን፣ ከአትሌት፤ አስቴር አወቀን፣ ጥላሁን ገሰሰን፣ ቴዲ አፍሮን፣ ከሙዚቀኛ፤ አበበ ባልቻን፣ ሰለሞን ቦጋለን፣ አልማዝ ሃይሌን፣ ከተዋናይ፤ ሼህ መሃመድ አላሙዲን ከሃብታም፤ እስክንድር ነጋን፣ ተመስገን ደሳለኝን፣ ከጋዜጠኛ ስብሃት ገ/እግዚያብሄርን፣ መሃመድ ሰልማንን፣ ከደራሲ ፤አበባዉ መላኩን እና በዉቀቱ ስዩምን ከገጣሚ፤ ያደነቅን ከሃገር ወጥተንም ማንቺስተር እና አርሴናልን ከክለብ፣ ማይክል ጃክሰንን- ከሙዚቃ ፣ሸዋዥነገርን ፣ዊልስሚዝን፣ ራነቦን- ከተዋናይ፤ ሮናልዶን ፣ሜሲን እና ሮኒን ከኳስ ተጫዋች፤ የደገፍን ያደንቅን እንዲሁም ከምናደንቃቸዉ ዉስጥ ስብሃት ሲሞት ያለቀስን፤ እስክንድር ነጋ ሲታሰር ያዘንን፤በዉቀቱ ስዩም አጉል ቀልድ ቀልዶ ሲደበደብ ያየን ፤የሰማን የመጀመሪያዎቹ ዉልዶች ነን፡፡
120 የሚባለዉ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ሲቀር የተበሳጨን፤ ኢቲቪ ፕሮግራሞችን በብሄር ከፋፍሎ ሲያቀርብ ያየን እና ሰዉ ለሰዉ ድራማን በማሰታወቂያ ብዛት እየተበሳጨን ያየን ፤ኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ የሰማንዉን ዜና ድጋሚ በቴሌቭዥን ያየን በfm የደገምን፤ በኢቲቪ ዉሸት ያዘንን፤ ለአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ የምታካሂደዉን ጨዋታ ለማየት ከክፍለ ሃገር አዲስ አበባ የሄድን፤ ለ8 ሰዓት ጨዋታ ሌሊት 11 ሰዓት ወረፋ የያዝን፤ ኢትዮጵያ ከ39 አመት በኋላ ለአፈሪካ ዋንጫ ስታልፍ ያየን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
ከሳይንስ እና ከሃይማኖት ማን ይዋሻል ብለን የተከራከርን፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ የፀሃይ ግርዶሽ ይከሰታል ተብለን መነፅር ይዘን ትምህርት ቤት የሄድን፤8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ፣ 10ኛ እና12ኛ ክፍል ማትሪክ ፣ኮሌጅ እና ዪንቨርሲቲ ሲኦሲ፣ የተፈተንን፤ ስራ ፈልጋችሁ ግቡ ወይም ስራ ፍጠሩ ተብለን የተመረቅን ፤ተደራጁ ተብለን የተደራጀን፤ ስራ በማጣታችን መንግስትን የተሳደብን፤ የመጀመሪይዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
በማንቺስተር እና በአርሴናል ጨዋታ ቁማር የተበላላን፤ የተደባደብን፤ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን ፎቶ አስይዘን ቀዳዳ የተጫወትን፤በህንድ የፍቅር ፊልም የተዋደድን ፤ያለቀስን፣ ለፍቅረኛችን የጋበዝን፣ ለተከታታይ ፊልም ገንዘባችንን የጨረስን፤ የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
አዲስ አድማስን፣ አዲስ ታየምስን፣ ሪፖርተርን፣ አዲስ ነገርን፣ ሮዝን፣ እንቁን ፣ያነበብን ፤ተወዳጆቹ ጋዜጦች እነ ፍትህ፣ አዲስ ታይመስ እና አዉራንባ ታይመስ ያነበብን፤ ሲታገዱ ያየን፤ የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡ መቶ ብር ዘርዝረን ለታክሲ ብቻ ጨርሰን ወደ ቤታችን የገባን ፤መቶ ብርን አመድ፣ ሃምሳ ብርን ቢጫ፣ አስር ብርን ዴች፣ ሃምሳ ሳንቲምን ቼላ፣ ሃያ አምስት ሳንቲምን ቹንክ፣ ብለን የጠራን ልብስን ልባብ፣ ጫማን ሾዳ፣ ገንዘብን መላ ፣ዘበኛን ዘቡሌ፣ ፖሊስን ዛፓ፣ ፍቅርን ፎንቃ፣ ፍቅረኛን ቺክ ብለን የጠራን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
የዳንኤል ክብረት ትዉልዶች ትዝብታችንንም መስማት ከፈለጋችሁ እናንተ ያስወሰዳችሁትን የአክሱም ሃዉልትንም የእኛ ትዉልዶች ናቸዉ ያሰመለሱት፡፡ይህንንም ለመታዘብ የበቃን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
የእኛ ትውልድ እኮ ሌላም ሌላም ታሪክ አለዉ
 እውነትም እነ ዳንኤል ክብረት የመጨረሻዎቹ እኛ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ነን
ዳንኤል ክብረት የእናንተ ዘመን ትውልዶች አቸነፈ እና አሸነፈ በሚሉ ቃላት የተጠዛጠዛችሁ የመጨረሻዎቹ ትውልዶች ናቸው። የእኛ ትውልድ ቢሆን ይህን ቃል ባክህ እንደፈለገህ ጥራው ይል ነበር። እንቀጥልማ
እኛ የ1980/90 እና 2ሺዎቹ ትውልዶች ኤፍ ኤሞቻችን እንደ አሸን ሲበዙ ያየን ቻናል እየቀያየርን የምንሰማ፤ አንድ የቴሌቨዥን ጣቢያ ያለን ምርጥ ትዉልዶች ነን፡፡ ከወገናችን የኑሮ ሁኔታ ይልቅ የአርሴናል እና የማንችስተር ጨዋታ፤ የሪሃና ከባሏ መፋታት፤ የሜሲ የጫማ ቁጥር፤ የሞሪኖ ንግግር፤ የሌዲ ጋጋ ጥፍር መቆረጥ፤ የሚያሳስበን ከእኛም አልፎ መገናኛ በዙሃኖቻችንንም የሚያስጨንቅ የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡ እኔ አዉቅልሀለሁ ተብለን የኖርን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡ አኛ እኮ ምረጥ ባለ ታሪኮች ነኝ፡፡ ከክፍለ ሃገር አስተዳደር ወደ ብሄር አስተዳደር ገብተን ምርጥ ብሔርተኛ የሆንን ሰዎች ነን፡፡ የእናንት ትዉልዶች መሬት ለአራሹ፤ ሰብአዊ መብቶች ይከበሩ፤ የመናገር ነፃነት ይከበበር እና የመሳሰሉትን መፈክሮች ይዛቸሁ ስትጮሁ እኛ እኮ ለሆዳችን እንድናስብ ተደርገን ቀበሌ ተሰልፈን እንድንዉል የተደረግን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡ እኛ እኮ ዪኒቨርሲቲ ገብተን ስለሀገራዊ ጉዳይ ልናዉቅ ቀርቶ ስማችንን በእንግሊዝኛ መፃፍ እንኳ የተሳነን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡ እኛ ታሪክ ሲፈጠር ቁጭ ብለን ያየን፤ በብሄር መካከል ወንድማማችነትን የሚፈጥር ታሪክ ፈልስፈን ሃዉልት ያሰራን ፤ ታሪክ አዋቂዎቻችንን ያጣን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡ እኛ እኮ ሌላ ነን፡፡ ሀገር እና ህዝብ ብሎ የሚጮኽን እስር ቤት የምናጠራቅም የመጀመሪያዎቹ ትውልዶች ነን፡፡ እኛ እኮ ሌባን ሙሰኛ ብለን ቃሉን አለዝበን እንዲሰርቅ ያበረታታን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን ፡፡ እኛ እኮ ሱሪያችንን ዝቅ አድርገን የዉስጥ ሱሪያችንን እያሳየን የምንሄድ፤ጠጉራችንን አንጨብርረን፤ ሹርባ ተሰረተን ወንድነታችን የጠፋን የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ነን፡፡ እኛ እኮ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ይፈቀድ ብለዉ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሰዎችን ያየን፤የባንዲራን ጨርቅነት የተቀበልን፤ ትርጉሙ የጠፋብን፤ ሀገር ማለት የሚያስነዉረን፤ ጠብበን የተሰራን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን ፡፡ እኛ አኮ 11 ከመቶ እድገት አስመዝግበን ከ5 ሚሊየን በላይ ህዝብ የተራበብን፤ከመቶ አመት በፊት የነበረዉን ባቡር ከተማችን ዉሥጥ ስራ ያስጀምረን ፤ አስጀምረንም የመጀመሪያዉ ባቡር ብለን የፎከርን የታሪክ ባለ እዳዎች ነን፡፡ ለምን? እንዴት? ወዴት? ብለን መጠየቅ የሚያስፈራን በፈረስ የምንሳብ ጋሪዎች ነን፡፡ እኛ አኮ በህዝብ ጉልበት እንድን ሰዉ ጀግና የምንል፤ ራዕይ የሌለን የሌላ ሰዉ ራዕይ የምናስፈፅም የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን ፡፡
እኛ እኮ ከእነ ዳንኤል ክብረት ዘመን ትዉልዶች እንለያለን፡፡ እናንትተ የመጨረሻዎቹ እኛ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ነን፡፡ የእኛ ትውልድ አኮ ለሽርፍራፊ ገንዘብ በወገኑ ላይ የፖለቲካ ሴራ የሚሸርብ ወገንተኛ የሆነ የመጀመሪያ ትዉልድ ነዉ፡፡
እኛ እኮ አንድ ፓርቲ መቶ በመቶ ሀገራዊ ምርጫን ሲያሸንፍ ያየን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡ እኛ በ1 ለ 5 ፤ በልማት ቡድን፤ በሴል እና በህዋስ የተደራጀን ግን ደግሞ መደራጀት ያልተፈቀደልን ፤ መንግስት እና ሃይማኖት እርስ በእርሳቸዉ ጣልቃ አይገቡም ተብለን የተማርን ግን ደግሞ ለመንግስታዊ በዓል ታቦት የምናወጣ የመጀመሪዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡ መስቀል እና አረፋ በዓላትን ስናከብር የሃይማኖት አባቶቻችን ‹‹ይህንን በዓል ስናከበር ለየት የሚያደርገዉ ጠቅላይ ሚኒስተራችን የልደት በዓላቸዉን ባከበሩበት ማግስት በመሆኑ ነዉ›› ማለት የሚዳዳቸዉ መሆኑን ያየን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን፡፡
ኢትዮጵያ የ100 አመት ታሪክ ነው ያላት ተብለን ታሪክ ተንሻፎ የተማርን፤ ቁጥር የሚምታታብን፤ ከባህላችን ይልቅ ለፈረጅ አጉል ልምድ ያጎበደድን የመጀመሪያዎቹ ትውልዶች ነን።
እኛ የወደፊት ህይወታችንን ለማስተካከል ከምንሮጥ ይልቅ የሁዋላውን ታሪክ ለማጥፋት የምንጥር ህልም የሆንን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን ።
ስኩዋር ዘይት እና ዱቄት ከቀበሌ ተሰልፈን የገዛን፤ ነፃ ገበያ ተብሎ ስኩዋር ሲሸጥ የተገኘ ሰው ሲታሰር ያየን፣ የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን ።
እኛ በራሳችን ህዝብ ላይ ድራማ የምንሰራ ድራማ የሆንን የመጀመሪያዎቹ ትዉልዶች ነን የእነ ዳንኤል ክብረት ትዉልዶች ደግሞ የመጨረሻዎቹ

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me