Search This Blog

Sunday 5 June 2016

08 08 08 08:08 ማላ እና ሞቴን አገጣጠመዉ



08 08 08 08:08 ገንዘብ ስላልሰጣችሁኝ ስማችሁን ለማጥፋት የፈጠርኳት ሰዓትና ቀን ናት
     (አዲስ መኮንን)


አንዱ ወዳጄ 5ኛ ፎቅ ከሚገኘዉ ቢሯችን መጣና ዩኒቨርሰቲዉ የኪነጥበብ ሰዎችን የትም በተናቸው እኮ  አለኝ፡፡
"የቱ ዩኒቨርሲቲ" ብየ ጠየኩት
"ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ነዋ" አለኝ። የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ከጠረጴዛየ ላይ እየወረወረልኝ። አነበብኩት።  የፊደል ገበታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የፍኖተ ንባብ አዘጋጆች የፍቅር እስከ መቃብርን 50 ዓመት በዓል ለማክበር አርቲስቶችን ሰብስበው ወደ ጎጃም ተጉዘዋል። "ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሊቀበለን ቃል ገብቶ የትም በተነን" የሚል ወቀሳ ነው። እንዴት ሊሆን ቻለ ብየ ትንሽ አንሰላሰልኩ። ከመፍረዴ በፊት ማረጋገጥ ነበረብኝ። ወዲያው አንዱ ከሚኒሚዲያ ያልዘለለ ጣቢያ ላይ ጉዳዩ እንደተወራ ሰማሁ። ለዚየውም 12 ደቂቃ ያክል አውርተውበታል አሉኝ። በጣቢያው እምነት ባይኖረኝም አዲስ ዘመንን ለማመን ተገደድኩ። የሆነ ስህተት ተፈጥሮ ችግሩ አጋጥሟል ብየ ደመደምኩ።
    ግንቦት 27 እና 28 የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ባዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ እንድሳተፍ ተጋበዝኩ። በአስገራሚው አውደ ጥናት ላይ በመጋበዜ መደሰቴን ገልጬ ለጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለዶክተር ስማቸው ጥይቄውን አቀርብኩላቸው። "እንዴት ቃላችሁን አጥፋችሁ ልዑካን ቡድኑን አንቀበላችሁም አላችሁ" አልኳቸው። ዶክተሩ ፈገግ ብለው መለሱልኝ። በፈገግታቸው ውስጥ አንዳች ንዴት ይተናነቃቸዋል።" ስፖንሰር እንድናደርጋቸው ደብደቤ ፅፈውልን መልስ ስላልሰጣናቸው ነው። ሲጀመር እኛ የባህል ማዕከሉ ትልቅ አውደ ጥናት ስላለው አንድ ጋር እንስራ ብለናቸው ነበር" አሉኝ። ዶክተሩ በስም ማጥፋቱ መናደዳቸው እያሰበቀባቸው ሄደ። "እንዲያውም እስኪ እሺ ያላቸው አካል ካለ ይምጡ" አሉኝ።
    የራሴን የማጣራት ስራ መስራት ነበረብኝ። የአዲስ ዘመንን ድህረ ገፅ ጎበኘሁ። አነበብኩት። ዩኒቨርሲቲውን ስፖንሰር ጠያቂው የፍኖተ ንባብ ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ አቶ አንተነህ ከበደ ነው። ፅሁፉን የፃፈው ደግሞ ዋለልኝ አየለ ነው። እኔ ግን በዋለልኝ ስም እንዲታተም ተደረገ እንጂ ሴራዋ የአንተነህ ነች። ምክንያቱ ደግሞ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሃዲስ አለማየሁ የተሰየመ የባህል ጥናት ተቋም ስላለው በሃዲስ አለማየሁ ስም ብንሄድ እና ገንዘብ ብንጠይቅ አናጣም ብሎ ተነስቶ ሳይሳካ በመቅረቱ ነው።
        ፅሁፉን እያጣቀስን እንመልከት። " ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሲመሠረት ሀዲስ አለማየሁንም ለመዘከር ተብሎ እንደነበር ዩኒቨርሲቲው ቢዘነጋውም ብዙ ሰዎች ያስታውሱታል ብዬ አምናለሁ።" ይላል። የትኛውም ዩኒቨርሲቲ ሲመሰረት ሶስት ዓላማዎችን ማለትም መማር ማስተማር፣ጥናትና ምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሉትን ይዞ እንጂ ግለሰብን ወይም ድርጅትን ለመዘከር ተብሎ ወይም ሁለተኛ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ የለም። ፅሁፉ ሳተ። በርዕሱ ላይ 08 08 08 08:08 ላይ ነው ነገሩ ገጠመብን ያሉት። 07:50 ደጀን ደረስን ካሉ 8:08 እንዴትም ማርቆስ አይድርሱም። ቢበዛ ሉማሜ ይደርሱ እንደሆን እንጂ።(ምናለ ድምር ላይ እንኳ ጥሩ ማጭበርበር ቢያደርጉ) እና እንዴት ሆኖ ነው ዩኒቨርሲቲው ሃዲስ አለማየሁ ምኔም አይደሉ ብሎ ፕሮግራሙን ሰረዘብን ብለው ሊሉ የቻሉት። በዚህ ደቂቃ እንዴት አወቁ? ደጀን ደረሰናልና ተቀበሉን ብለው ስልክ ደውለው? ወይስ ለወሬው ድምቀት የተፈለሰፈች ቀመር? እውነቱን እናውራ ከተባለ ለወሬ ማድመቂያ የተፈጠረች ትመስላለች።
    ሌላው አንድም የዩኒቨርስቲውን አመራር ጠቅሰው ሊነግሩን አልፈለጉም።እከሌ እንዲህ ብሎናል አላሉም። ለምን? የጋዜጠኝነት ሙያስ በእውር ድንብር የሚመራ ነው? አንድ ፅሁፍ ባለቤት ይኖረዋል። እነ አንተነህ የጥቅም ግጭት የጋዜጠኝነቱን ሙያ አሳታቸው እንበል። አዲስ ዘመን እንደ ሙያ ፅሁፉን ባላንስ አልተደረገም። ስለምን አልተደረገም? አዲስ ዘመን ለምንስ እንደ ጋማ ከብት ሳያመነዥክ አተመው።
       በመጨረሻ ስለምን ዩኒቨርሲቲው ግቢ ደርሰው አንድ ሰው እንኳ ለማናገር አልሞከሩም? አንድን ትልቅ ተቋም ያለምንም ማስረጃ ስም ማጥፋት ወንጀል ነው? በአሁኑ አውደ ጥናት ላይ ስሳተፍ ብዙ ነገሮችን አይቻለሁ። ሌላው ቀርቶ ለአርቲስት ዮሃንስ አፍወርቅ (ፍቅር እስከመቃብር ላይ ዋሽንት አናጋሪው) 160 ብር አውጥቶ ቪሲዲ አዘጋጅቶ ሸጠዉጠቀሙ ብሎ የሰጠ ተቋም ነው። ስለ ሃዲስ አለማየሁም 4 በላይ ጥናታዊ ፅሆፎችን በአንድ አውደ ጥናት ያስኬደ ተቋም ነው። እንዲያዉም ከሀዲስ አለማየሁ ዉጭ ሌሎች አይዘከሩም ወይ የተባለ ነዉ፡፡
        እነ አንተነህ እንደሚሉት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሀዲስ አለማየሁ ጉዳይ « ለእኔ ምኔም አይደለም» ቢል ኖሮ በስማቸው የባህል ማዕከል አይከፍትም ነበር፤ ሃውልት አያሰራም ነበር፤ ይህንን ያክል አውደ ጥናትም አያዘጋጅ ነበር። ገና ለገና የሚዲያውን እድል አገኘሁ ተብሎ የጋዜጠኝነትን ሙያ መጣስ አስነዋሪ ነው። አዲስ ዘመንም እንዲሁ።

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me