Search This Blog

Saturday 14 January 2017

ኮሌጅ እና ትዝታ
ትዝታ 2፦ ዘ ብሄረ ዩኒቨርሲቲ
@@@@@@@@@@@
ብሄር የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ያወኩት ዩኒቨርሲቲ ነው። ቀድሞ የማውቀው እከሌ ዘ ብሄረ ቡልጋ፣ እከሌ ዘ ብሄረ ዘጌ ምናምን በሚል ነው። ስለዚህ ብሄርን በሆነ ሰፈር ስም ነበር የማውቀው። ይህንን ነገር ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ፅፈውት በዚህ ዓመት አነበብኩት። ዩኒቨርሲቲ እየቆየሁ ስመጣ ብሄር ለሆነ ቋንቋ ተናጋሪ እንደተሰጠ ገባኝ። አማሪኛ ተናጋሪው አማራ፣ኦሮምኛ ተናጋሪው ኦሮሞ፣ ትግሪኛ ተናጋሪው ትግሬ፣ ጉራጊኛ ተናጋሪው ጉራጌ.... በሚል ተተረጎመ።እንዲህ ከሆነ ደግሞ ቋንቋ እንጂ ብሄር የሚባል ነገር የለም የሚል ድምዳሜ ውስጥ ገባሁ። በነገራችን ላይ አሁንም ቋንቋ እንጂ ብሄር የለም የሚል አስተሳሰብ ነው ያለኝ።
አማራ ልማት ማህበር፣ ኦሮሞ ልማት ማህበር፣ትግራይ ልማት ማህበር የሚሉ ማህበራት መጡና ገንዘብ አዋጡ መጣ። የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ወደ ግቢው ሲገቡ ተቋሙ ራሱ አቀባበል ያደርጋል። ከዚያ ዝቅ ሲል ደግሞ በትምህርት ክፍል ተማሪዎች "እንኳን ደህና መጣችሁ" ይባላሉ። ቆይቶ አስቀያሚው አቀባበል መጣ የአማራ ተወላጆች የኦሮሞ ተወላጆች የትግራይ ተወላጆ አቀባበል እየተባለ ከግቢው ውጪ ፕሮግራሞች መዘጋጀት ጀመሩ። ፑል ቤት እውላታለሁ እንጂ እንዲህ ያሉ ፕሮግራሞች ላይ መገኘት አይመቸኝም። ከቡዘና መልስ ያን ግዜ ብሄር የሚባለው የቋንቋ ክፍፍል ፍንትው አለልኝ። ትምህርት ቤት አይደል!!
የእኛ ክፍል በስልጣንም በነጥብ ሰቀላም ከፍተኛ ፊክክር የነበረበት ክፍል ነው። በየአመቱ መፈንቅለ ነጥብ ተደርጓል። ወዳጄ ምስክር አንደኛ አመት ላይ ሰቀለች።ሁለተኛ አመት ላይ ወዳጄ ያየሰው ካለምንም ደም መፍሰስ የተሳካ መፈንቅለ ነጥብ አድርጎ ሰቀለ። አንደኛ አመት እስጢፈኖስ የሚል ፊልም ሲሰሩ ስለነበር ለዚያ ነው የተዘረርኩት እያለ አሁን ድረስ ሲቆጭ ሰምቻለሁ። ያየሰው ግዕዝ የማይችል ነገር ግን እኔን ግዕዝ ያስኮረጀ ብቸኛ ሰው ነው።ካገኛችሁት ና "C"ህን ውሰድ በሉልኝ።ሶስተኛ ዓመት ላይ እኛም ፊልም ጀምረን የምማርበት ክፍል ሁላ ጠፍቶብኝ ነበር። ተመርቀን ከወጣን በኋላ ይህንን ፊልም ያየች የ8 ዓመት ልጅ ኮብል ስቶን ስጠርብ አይታ "ቱ ሞት ይሻላል። ፊልም እየሰራህ ድንጋይ ትጠርባለህ?" ብላኛለች። ከዚያ ወዲህ የካሜራ ፎብያ ተጠናወተኝ።
ዩኒቨርስቲያችን አሉኝ የሚላቸው 3 በጣም ዝነኛ ሰካራሞች ነበሩ። አንደኛው አንድ ቀን እኔ ፑል ቤት አምሽቼ እሱ ደግሞ ጠላ ቤት አምሽቶ ወደ ግቢ ሲገባ ተገናኘን። ግቢው ውስጥ ግንባታ ይካሄድ ስለነበር ትልቅ ጉድጓድ አለ። የተወሰነ ውሃም አለበት። ወደ ግቢ የሚያስገባውን ዋናውን መንገድ ትቼ ወጣ አልኩና ጉድጓዱን ዘልየ ተሻገርኩ። ልጁ በጣም ከመስከሩ የተነሳ (እፅም የወሰደ ይመስለኛል) እኔ ተንደርድሬ ዘልየ ስሻገር ከትትት ብሎ ሳቀብኝ እና
"ከዚያ ድረስ የተንደረደርክው ይቺን ለመዝለል ነው?" አለኝ። አሳሳቁ በጣም ያበሳጫል። እጁን ሆዱ ውስጥ ወሽቆ አጎንብሶ ነው የሚስቀው።ክክክክ..
"እኔማ ራመድ ብየ ነው የምሻገራት" ብሎ አንደኛው እግሩን አንስቶ ውሃው ውስጥ ቸርፏ አለበት። በውሃ እና ጭቃ በስብሶ እየተንዘረዘረ ወደ መኝታ ክፍሉ ገባ። ጠዋት ሱሪውን ሲያጥብ አገኘሁት።
አንደኛው ጓደኛችን ዶርሙ ውስጥ የሄድፎን ብጥስጣሽ ቀጣጥሎ ከመኝታው ዘንግ ጋር አገናኝቶ ሲደንስ ተገኝቶ "ፈታ" ተብሎ ተወራበት። ያንን ለምን እንዳደረገ እስከ አሁን ባይገባኝም ተመርቆ በመንግስት መስሪያ ቤት ኋላፊ ሆኗል። በነገራችን ላይ ሰቃይ የሚባል ተማሪ እና መንግስት ፈፅሞ እንዲታማበት የማይፈልግ ልጅ ነው። ዶርም ውስጥ የፖለቲካዊ ጉዳዮች ተነስተው ክርክር ከተደረገ እና ከተሸነፈ "እናታችሁን ልቀፍላችሁ" ብሎ ተነስቶ ይወጣል።
3ኛ አመት ተማሪ እያለን የውሃ ቀንን ድምቅ ባለ ሁኔታ አክብረን ማታ ረብሻ ተነሳ። ረብሻው የተነሳው ሃሙስ ቀን ስጋ ሳይቀርብ ቀርቶ ለእሁድ በመቀየሩ እና እሁድ እለትም ሳይቀርብ በመቅረቱ ነው። በጣም የሚያበሳጨው ግን ብጥብጡን ያስነሳው የውሃ ቀን መከበሩ ነው ተብሎ ተሳበበ። ጉዳዩ ደግሞ ቀጥታ ወደ እኛ ጋር ይመጣል- ወደ ጂሲ ኮሚቴው። በራሳቸው ጥፋት እንደሆነ ተማመንን። ማታ የመጀመሪያዎቹ አምስት ልጆች እስር ቤት ገባን።
እኔ እራት ለመብላት ከዶርም ወደ ውጭ ስወጣ ኮሊደር ላይ ተይዤ (ከነ ችጋሬ)
ከድር ከሽንት ቤት ሲወጣ ተይዞ
ባላቶሊ ከውጭ ወደ ግቢ ሲገባ በእንግሊዝኛ መልስ መልሶ
አንዱ ጩቤ ኪሱ ተገኝቶበት
አንዱ ተማሪ ያልሆነ የግቢ ሳር አጫጅ ግቢ ውስጥ ይዘውት (ምስኪን)
እኛ ከዚያ በኋላ የሆነውን ማየት አልቻልንም። እኛ ያለጥፋታቸው ነው የታሰሩት ተብለን ስንለቀቅ ባለጩቤው ቀረ። ስንወጣ ጓደኞቼ ወሬ አስወርተውብኝ ሲናፈስ አገኘሁ። አዲስ ሲገረፍ "ታንክ ዶርም ደብቄያለሁ" ብሎ አለ ብለው ተወራብኝ። ያሳለፍንው ግዜ እንዴት ደስስስ ይላል መሰላችሁ!! ...በናታችሁ ወደ ዩኒቨርሲቲ መልሱን

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me