Search This Blog

Sunday 30 July 2017

የምርጫው መንገድ


ባለፈው እንደባላባት አድርጎን የቤተመንግስት ጠጅ መጠጣት አለብን ብለን ወደ አንኮበር ቤተ መንግስት ጉዞ ጀመረን ነበር። ከደብረ ብረሃን አንኮበር ያለው ፒስታ መንገድ መኪናችንን እያርገፈገፈ ውልቅልቅ ሊያደርጋት ቃጣው። ለመዝናናት መሄዱ ቀርቶ መንገዱ ቀጥቅጦ ቀጥቅጦ መጉላላታችን ባሰ። ዝናብ ተጨመረበት። እስኪያባራ ብለን መኪናችንን ጥግ አስይዘን ቆምን። ዝናቡ አባርቶ ጉዞ ስንጀምር ከአንኮበር በኩል ህዝብ ጭኖ ለሚመጣ ተሽከርካሪ ቦታ እለቃለሁ ብሎ ዳር ሲይዝ የመኪናችን የቀኝ የኋላ እግር ጭቃ ውስጥ ሰመጠ። እግሩ ብቻውን እየተሽከረከረ ወደ ውስጥ እየጎደፈረ መንቀሳቀስ በአባቴም የለብኝ አለ። ይባስ ብሎ የፊት እግሩንም ጎትቶ ጭቃ ውስጥ ከተተው። ሹፌራችን "እኔ ድሮም መንገዱ የማይሆን መንገድ ነው ብየ ነበር" ምናምን እያለ ማለቃቀስ ጀመረ። በእርግጥ መንግዱ ውሃ ሽርሽሮት፣ አንዳንድ ቦታ ተቆፍሮ ውሃ ሞልቶት ያለ አስጠሊታ መንገድ ነው። ፀሃይ ወጥቶ አየሩ ሞቅ እስኪል ተቀመጥንና ሁለቱንም እግር በየተራ በክሪክ አንስተን ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ እንዲቀመጥ ካደረግን በኋላ ጭቃው ላይ ድንጋይ ስንደረድር ሁለት ገበሬዎች አገዙን። አንደኛው ገበሬ "አይ ይሄ የምርጫ መንገድ" ብሎ አዘነ። ሹፌራችን አሁንም ይነጫነጫል። ሰውየውን "የምርጫ መንገድ ምን ማለት ነው?" አልኩት። ፈገግ አለ።
"ይሄ መንገድ ምርጫ በመጣ ቁጥር ሊሰራ ነው ቲባል፣ ምርጫ በተቃረበ ቁጥር እገሌ ተሚባለው ኮንትራተር ጋራ መንገዱ ሊሰራ ስምምነት ተፈረመ ቲባል ይኸው ዛሬም አለ፣ እና እኛ ግራ ቢገባን ግዜና "የምርጫ መንገድ" አልነው። ለምርጫ መኧስኧሻ አድርገውት አረፉ። እንዳው ታዘበኝ ወንድሜ ተኧጣዩ ምርጫ ላይም ሊሰራ ነው ባይባል፥ ተምላሴ ነጭ ጠጉር ትነኧል። ቱ" አለኝ። ሹፌራችን ንጭንጩን ረስቶት
"ባለፈው አንዱ ጓደኛየ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው" አለና ወሬ ሊያዳንቅ አፉን አሞጠሞጠ። ያ ነገረኛ ጓደኛችን
"ብዙ ገንዘብ እሰጥሃለሁ ቢልህ ጥሩ ነው" አለና ወሬ አቆረፈደበት። እኔ ነጭንጩን በዚያውም ይርሳው ብየ
"እሺ...." ብየ ወሬ አስጀመርኩት።
"በርካታ የመሰረት ድንጋይ ሊጣል ስንት አመት ቀረን? ብሎ ጠየቀኝ። ማለት የፈለገው ግራ ስለገባኝ ምን አይነት ጥያቄ ነው ብየ ተሳለኩበት። ባክህ ቀጣዩ ምርጫ መቼ ነው ለማለት ነው አለኝ። ይህንን ያነሳሁት የምርጫ መንገዱ ቢነሳ ግዜ ነው!"አለና አጫወተን።ወሬውን እህ ብለን ስለሰማንለትም ኩራት ቢጤ የተሰማው ይመስላል። ሁለቱም አርሶ አደሮች ጥርስ በጥርስ ሆኑ። ሁላችንም እየተሳሳቅን የጠጁን ፕሮግራም ሰርዘን ወደ ደብረ ብረሃን ለመመለስ ተስማምተን ተመለስን።እውነትም የምርጫ መንገድ!! እኔ እንኳ ፋና የነበርኩ ግዜ ሁለት ግዜ መንገዱ ሊሰራ ነው ብየ ዜና አንብቤያለሁ። ምነው ምላሴን በቆረጠው ነበር አይባል ነገር!? ቱ!!

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me