Search This Blog

Sunday 30 July 2017

የሰርግ ወሬዎች


እሁድ አለት (የአላዩ ገረመው እና የኤልሰቤጥ ሹምየ ሰርግ ነበር) ሙሺሪቷን ይዘን ከሙሽራው ቤተሰቦች ቤት ገጠር ሄድን። ከመኪና ወርደን 30 ደቂቃ ያክል የእግር መንገድ አለው። ማታ ጭቃ ስላልነበር ያለምንም ችግር ቢመሽም ገባን። ሰኞ እለት ስራ የነበረን ሰዎች 12 ሰዓት ተነስተን ወደ ደብረ ብረሃን ጉዞ ጀመርን። ሌሊቱን የዘነበው ዝናብ ጭቃ ሆኖ ጫማችንን እያስቀረ በጣም ተቸገርን። ያለን አማራጭ ጫማ ማውለቅ ሆነ። ጫማችንን አውልቀን ጉዞ ጀመርን። መሬቱ የጤፍ መሬት እና በጣም ለስላሳ ስለነበር ዋናውን መንገድ ትተን በታረሰው መሬት ላይ መሄድ ጀመርን። መሬቱን ስንረግጠው ፍራሽ የረግጥን ያክል ስምጥ ስምጥ ሲል በጣም ደስ ይላል። የታረሰውን መሬት ጨርሰን ፒስታው መንገድ ላይ ስንወጣ ጠጠሩን መርገጥ ተሳነኝ። ፒስታ መንገዱን አቋርጬ እግሬን ለመታጠብ ውሃ ወዳለበት ቦታ ለመሻገር ስሞክር ጠጠሩ ከቅዝቃዜው ጋር ውስጥ እግሬን ሲወጋኝ ህመሙ ጭንቅላቴ ድረስ ተሰማኝ። ሽምቅቅ ሽምቅቅ እያልኩ እንደምንም ተሻገርኩት። ጠጠሩ ከብርዱ ጋር አሠከረኝ ማለት ይቻላል። ቀጥታ አዕምሮየ ውስጥ የመጣልኝ ስለ ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ያነበብኳቸው መፀሃፍት ናቸው። በባዶ እግር በብርጭቆ ስብርባሪ ላይ ይሄዱ እንደነበር ምስክረነታቸውን የሰጡ ሰዎች ስቃይ መጣብኝ። ለዚህ ጠጠር እንዲህ የሆንኩ እንደዚያ ያለ አደጋ ቢገጥመኝ ብየ አሰብኩት። ዘገነነኝ። የፓለቲካል ሳይንስ ትምህርት የመማር እቅዴን ወዲያውኑ ሰረዝኩት። welcome መሃይምነት።
ሌላ ወሬ
የመልሱ ዕለት ሴቷ ቤት ልንሄድ ስንነሳ በጉ የት እንደገባ ጠፋ። መኪና ላይ ተጭኖ ነበር አለን አንዱ ሚዜ። መኪናው ላይ የለም። እኔና ብረሃኑ ደብረ ብረሃን ስለነበርን መኪናው ላይ ጭነው ይምጡ አይምጡ የምናውቀው ነገር አልነበረም። በቃ በጉ ጠፋ። ሰዓቱ ከምሽቱ 1፡30 ሆኗል። 2፡00 ላይ ሙሺሪቷ ቤትሰቦች ቤት መድረስ አለብን። በግ ሳይያዝ እንዴት ይገባል? እኔ በጉ ከሌለ ታመምኩ ብየም ቢሆን እቀራታለሁ እንጂ ዳቦ ብቻ ይዘን እየጨፈርን አንገባም ብየ ለራሴ ቃል ገባሁ። በጉ ከመኪናው ላይ በረሮ ነው የጠፋው ተብሎ ተቀለደ። የሙዜውን ከርፋፋ በለው በአካፋ እንዲሉ 1ኛ እና 2ኛ ሚዜዎቹን በአካፋ ብጠርጋቸው ምንኛ ደስ ባለኝ። አጠብቂኝ ውስጥ ገባን። በ30 ደቂቃ ውስጥ ስልክ በዚየም በዚህም ስንደዋወል 3 ቦታ በግ ተገኘ። አንድ ቦታ ሄደን ገዝተን ስንመለስ በጉ ጠፋ በግ ፈልግልን ብየ የደወልኩለት ጓደኛየ መሲ ደወለልኝ። "የጠፋው በግ ምን አይነት ነው እኛ ሰፈር አንድ የተገኘ በግ አለ" አለን። ሚዜውን ደውየ
"ምን አይነት በግ ነው የጠፋው" ብለው እኛ ማግኘታችንን ስላወቀ ነው መሰለኝ
"እረስተንው ጭራሽ መቼ ገዛን!" አለንና አረፈው። ደግነቱ በጉን ስንገፍ ይህንን ከርፋፋ ሚዜ እጁን ቆረጥኩት እና ብድራችንን መለስን ተብሎ ታለፈ።
ሌላ ወሬ
የሙሽራው ቤተሰቦች ቤት የሄድን ቀን የእኛ ጭፈራ እና የአካባቢው ጭፈራ እንዴትም ሊገጥምልን አልችል አለ። የእኛ ጭፈራ አዲስ አበባ የሚዘወተረው እስክስታ አይነት ነው። እዚያ አካባቢ ያለው ደግሞ ጨፋሪዎቹ ጥንድ ጥንድ ይሆኑና ተራርቀው በእጃቸው በሃይል እያጨበጨቡ፣ ከእጃቸው ምት እኩል መሬቱን በአንድ እግራቸው እየመቱ እንዲሁም በእጃቸው በሚያጨበጭቡት እና መሬቱን በአንድ እግራቸው በሚመቱት እኩል "ህይይይ" ብለው እየጮሁ ነው የሚጨፍሩት። ጭፈራው በጣም ሃይል የሚፈልግ ነው። በአንድ ዙር ጭፈራ ፊታቸው ውሃ የፈሰሰበት እስኪመስል በላብ ይጠመቃል። እኔ ግን የጉሮሯቸውን ፅናት አደነኩኝ። ከደብረ ብረሃን የሄድንው ጦጣ ሆነን ቁጭ አልን። አንጉራጓሪው የሚደረድራቸው የወል ግጥሞች ግን እጅግ መሳጭ ናቸው።
"ስሙኒ ሰጥቻት ማታ ና ብላኝ
50ሳንቲም ሰጥቶ ከኋላ ቀማኝ" ይቺን ግጥም እዚያው ለግዜው የሰማኋት ግጥም ናት። ይሄ የሊብራሊዝም ቴዎሪ ነው። ብረሃኑ ድንቄ የምዕራባውያንን ፍልስፍና የእኛ ሃገር ቄሶች ቅኔ መሆኑን አስረግጠው የተናገሩበት አልቦ ዘመድ ትዝ አለኝ። ይሄ ግጥምም የእነ አሜሪካ የሊብራሊዝም ፍልስፍናና የዳርዊን አሸናፊው ይኖራል ቲዮሪ ነው።የሆነው ሆኖ ቁጭ ብለን የሃገሬውን ጭፈራ ስንኮመኩም አደርን ማለት ይቻላል። ከሚዜ ከርፋፋነት ወደ ሚዜ ጦጣ ሚዜነት

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me