Search This Blog

Sunday 30 July 2017

ከቴም እቴ

ከስራ ስወጣ ወደ ቤት የሚሸኘኝ ሹፌር ካለወትሮው ሌላ መንገድ መርጦ ውስብስብ ያለ ሰፈር ውስጥ ይዞኝ ገባ። ለምን እንደሆነ ስጠይቀው "እቃ ተቀብለን ወደ ቤት ላደርስህ ነው" አለኝ። ተስማማን። ወደ ሰፈር ልንደርስ ስንል ቁልቁለት ነገር ኑሮት እንደገና ዳገት ያለው ቦታ ገጠመን። ይቺን ለመውጣት ከታች መንደርደር ያስፍፈልጋል። ቁልቁለቷን ጨርሰን ዳገቷን ስንጀምር የመኪናው ሞተር ድርግም ብሎ ጠፋ እና ሚኪናው ወደ ኋላ ተመለሰ። ሞተር አስነስቶ አሁንም ሊንደረደር ሲል ሞተር ይጠፋበት ጀመር። በ3ኛው ሲወጣ የሼፌሩን እግር ፔዳል አረጋገጥ ማየት ጀመርኩ። ዳገቱን ሲጀምር ፍሪሲዮን ሳይረግጥ ፍሬን ቶሎ ሲይዝ እና ሞተሩ ጠፍቶ መኪናው ወደ ኋላ ሲመለስ አየሁ። ይሄ ጠፍቶት ነው ብየ ባላስብም "ውረድ እና እኔ ላስጣልህ" አልኩት። አይሆንም ብሎ ድርቅ አለ። "
እንዲያውም አንተም ስለደረስክ በእግርህ ወደቤት ሂድና ምሳህን ብላ እኔም መኪናውን ወደ ኋላ ወስጄ ጥግ አስይዤ እቃየን ልቀበል" አለኝ። ነገሩ ሁላ ባያሳምነኝም ተስማማሁ። ዳገቷን ወጣ ብየ ወደ ቤት መግቢያየ እጥፍ ስል ከየት መጡ ሳልላቸው የሆኑ ሰዎች አፋፍሰው መኪና ውስጥ አስገቡኝ። መጀመሪያ በጃኬታቸው አይኔን ሸፍነውኝ ነበር። መኪና ውስጥ በሆነ ጨርቅ ነገር አይኔን ብቻ አስሩና እጄን ወደ ኋላ በካቴና ነገር አሰሩኝ።አንዳቸውንም ማየት አልቻልኩም።
"ስንነግርህ አልሰማ አልክ አይደል?" አለኝ አንደኛው። መኪናው እየሄደ ነው። ወዴት አቅጣጫ እንደሚሄድ መለየት አልቻልኩም።
"እንዴየ ምን አደረኩ ቆይ? ምን ነግራችሁኛል? ልትዘርፉኝ ከሆነ ያው ያለውን ውሰዱና እኔን ልቀቁኝ" አልኩ ልቤ እየመታ።
"ሂድ!! የማትረባ። አንተ አሁን ምን ኖሮህ ነው የምንሰርቅህ?" አለኝ።
"ከአንዴም ሁለት ግዜ ሰው ላክንብህ። አንተ ግን አሻፈረኝ አልክ" አለችኝ አንዷ ሴት።
"ስለምንድነው የምታወሩት"ብየ ተበሳጨሁ።
"እሱን ስትገረፍ ታውቀዋለህ" አለኝ ከጋቢና በኩል የተቀመጠ ሰው፡ ሹፌሩ ይሁን አይሁን ግን መለየት አልቻልኩም። ወዴት እየወሰዱኝ እንደሆን ለመለየት ጥረት ባደርግም አልተሳካልኝም።
"አራት ኪሎ፤ አራት ኪሎ፤ ቦሌ፤ ቦሌ የሚል የወያላ ድምፅ ሰማሁ። ወዲያው መስኮቶቹን ሲዘጉብኝ ድምፅ መስማት ሳልችል ቀረሁ።
"እናታችሁን ልቀቁኝ" ብየ እሪታየን ሳቀልጠው አንዱ
"ዝም በል ክፍት አፍ" ብሎ ጨርቅ አምጥቶ አፌ ላይ ወተፈብኝ። እግራቸው ማስቀመጫ ጋር አስተኙኝና እግራቸውን አስቀምጡብኝ። የአንደኛው ሰው እግር ሸተተኝ። ወደ ላይ ልበልህ አለኝ። አፌ ታፍኖላልና በደንብ በማይሰማ ድምፅ
"እናትህንና ጫማህ ይሸታል" አልኩት ለመገላበጥ እየሞከርኩ። እንደመሳቅ አሉና
"ገና የሽንት ቤት ቀዳዳ ውስጥ አንገትክን አስገብቼ እረግጥሃለሁ" አለኝ። በጫማው ቆሻሻ ረግጦ ኖሮ
"ወርደህ ጥርገህ ና" ምናምን አሉት።
"ስንደርስ በዚህ በማይረባ ሰው ጃኬት እጠርገዋለሁ" አለ። መናገር አልቻልኩም። ምን እየተሰራ እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም። እንኳን ለማምለጥ ለመጮህ እንኳ እንዳልችል አድርገውኛል። ሹፌራችን እጁ እንዳለበት ጠረጠርኩ። ከቢሮ ስንወጣ ሌሎች ሰራተኞችን እግረ መንገዱን ይዞ ይወጣ የነበረ መኪና ማንንም መጫን ሳይፈልግ እኔን ብቻ ይዞኝ እንዴት ሊወጣ እንደቻለ ግራ ገባኝ። መንገዳችን ላይ ይወርድ የነበረ ሰውም "ይዘህኝ ሂድ" ብሎት "ወደ ሌላ ቦታ ነው የምንሄደው" ብሎ እምብይ ብሏል። የተቀነባበረ ነገር እንዳለ ገባኝ። እንዴት እንዲህ አሳልፎ ይሰጠኛል? ዝም ብየ ማሰላሰል ጀመርኩ። አወጣለሁ አወርዳለሁ፥ ምንም ጠብ የሚል ሃሳብ ጠፋ። ይልቁንም ቀኑ የተወለድኩበት ቀን መሆኑ የባሰ አባሳጨኝ። መኪናው የሚያንገራግጭ መንገድ ውስጥ ገብቶ 5 ደቂቃ ያክል ከተጓዘ በኋላ አንድ ግቢ ውስጥ ገባ።
"አውርዱት" አለ መኪና ውስጥ ያልነበረ ሰው ይመስለኛል። አውረደውኝ ግራና ቀኝ ይዘው ፀጥ ወዳለ ቤት ውስጥ ይዘውኝ ገቡ።
"መጀመሪያ ይገረፍ ወይስ ቃሉን ይስጥ?" አለ አንደኛው።
"ሱሪውን አውልቀን እንግረፈው" አለች አንዲት ሴት። 'ድሮም ሴት አይሆነኝ ወይኔ ጉዴ አለቀልኝ በቃ' አልኩ በውስጤ። አፌ ውስጥ ጨርቅ ተወትፎ "ምን አድርጌ ነው ማለት እንኳ አልቻልኩም።
"ከአፉ ላይ የወተፋችሁትን ጨርቅ አውጡለት" አለ። የአብዛኞቹ ተናጋሪዎች ድምፃቸው ጎርነን ያለ ነው። ሆን ተብሎ የተደረገ እስኪመስል።
"የህዳሴው ግድብ ከዳር እንዳይደርስ ከግብፅ ጋር አሲረሃል" አለቸኝ ያቺ ቅልብልብ። ልክ ቲያትር እንደሚሰራ ድምፁዋን የሆነን ሰው ለማስመሰል የሞከረች ትመስላለች። ከት ብየ መሳቅ ስጀምር በጥፊ አጋየችኝ።
"እናትሽ ት..." ብየ ጮኩባት። በውስጤ 'ይሄ አጉል ልማድ' ብየ በስድቤ ተፀፀትኩ። 'በቅሎ ማስሪያዋን በጠሰች ቢሏት ወዲያው አሳጠረች' ብየም ተረትኩ።
"እግሩን ወደ ላይ አድርጋችሁ ስቀሉልኝ" አለ አንደኛው።
"ቆይ ቆይ መጀመሪያ የኢሜል እና የፌስ ቡክ አካውንቱን ከነፓስወርዱ ይስጠን" አለና ወረቀት ማገላበጥ ጀመረ።
"ኢሜልክን ተናገር" አለኝ።
" እናንተ ማን ናችሁና ነው የምነግራችሁ?"
"ሰውነትህ እንዲተለተል ከፈለክ አለመናገር መብትህ ነው" አለና አንባረቀ። ወዲያው
"አንተ ልብሱን አውልቅልኝ። አንቺ አልንጋውን አምጪ" ብሎ አዘዘ። ደንዝዣለሁ። አንደኛው መጥቶ ጃኬቴን እና ቲሼርቴን አወለቀ።
"እሺ እሺ ልስጣችሁ" ብየ ተስማማሁ።
"ኢሜልክን ተናገር አለኝ"
"addismekonen@yahoo.com" አልኩት።
"ፓስዎርድ" አለኝ። ሳልመልስ ዝም አልኩ
"ተናገር እንጂ" አለኝ።
"a..."
"እየጠበኩህ ነው" አለኝ
"m...."
"ቀጥል ቀጥል " አለኝ። ያቺ ቅልብልቅ መጣችና
"አለቃ ምርመራውን አቁሙት ተበሏል፦ከበላይ" አለች።
"ተባለ እንዴ? ምን ይቀልዳሉ ግን? በቃ ልብሱን አልብሱና ፍቱት" አላቸው። አቋቋሜን አስተካክለው ልብሴን አለበሱና የሱሪየን አቧራ አራገፉልኝ። እጄንም ፈቱልኝ። ኮሌታየን አስተካከሉልኝ። ፀጉሬንም አበስ አበስ አደረጉና አስተካክለው አይኔን የሸፈኑበትን ጨርቅ አነስተው
"Happy Birth Day to you" በለው ቀወጡት። እየተበሳጨሁ ኬክ ቆረስኩ። ወደ ሞት እየተጠጋን እንደሆነ ለሚነግረን እድሜ ሞት ሞት በሸተተ "ሰርፕራይዝ" ተቋጨ። በጥፊ የመታችኝን ማርታን በኬክ ጠፍጥፌ ጣልኳት። "ድንቄም ሰርፕራይዝ!"

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me