Search This Blog

Sunday 30 July 2017

ኮለኔሉ መረጃ ከሰጡን ያምታቱብን


ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ "አጨራረሱ እንደ አጀማመሩ ድንገተኛና ያልተጠበቀ የሆነዉና ለመወሳት ያልታደለዉ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት" በሚል ሆርን አፍየርስ ላይ የፃፉትን ተከታታይ ፅሁፍ ከእልህ አስጨራሽ ንበት በኋላ ጨረስኩት። የፅሁፉ አጠቃላይ ጭብጥ ጦርነቱ በእኛ ድል አድራጊነት እንደተጠናቀቀ እና አሰብ የኢትዮጵያ ህጋዊ ይዞታ እንደሆነና መመለስ አለበት የሚል ነው። ፅሁፉን ሚዛናዊ ሆነው አንዳንዴም ወገን እያደረጉም ቢሆን የፃፉት እሳቸውም እንዳሉት የአሰብ ጉዳይ መነሳት መንግስትን ያበሳጫል እያሉ ደፈረው መፃፋቸው ለእኔ ተመችቶኛል። አንዳንድ እንደ ህዝብ በጅምላ በእውነትነት የፈረጅናቸውን እውነት "እውነት አልነበረም" ብለው ለማሳመን የሄዱበት መንገድ ግን ለአንባቢ በጣም አታካች ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በዚያ ላይ ፅሁፉ ውስጥ ሙሉ አንቀፅ እየተደጋገመ መገኘቱ ደግሞ በአንዳንድ ጉዳዮች የደከመውን አንባቢ የበለጠ ያበሳጫሉ። እስኪ ያምታቱብንን ነገሮች አለፍ አለፍ ብለን እንጥቀስ፦ ምናልባት ተጨማሪ መረጃ ሌላ ግዜ ሊጨምሩልን ይችላሉ ብለን ተስፋ በማድረግ።
#የጦርነቱ አሸናፊ፦ ሊደል ሃርት (Liddell Hart) “ድል የአሸናፊዉን ኢኮኖሚ ፣ወታደራዊ አቅምና ህብረተሰቡን የሚያደቅ ከሆነ ረብ የለሽ ነዉ” ይላል፡ ብለው በጠቀሱት ፅሁፋቸው ውስጥ አንባቢ የጦርነቱ አሸናፊ እኛ ነን ብሎ እንዲያምን ሲያስገድዱት ይታያሉ። በዚህ ብያኔ መሰረት አንባቢ እንዴት የጦርነቱ አሸናፊ ነን ብሎ ሊያምን ይችላል? ወይ ኢሳያሳን ከስልጣን አላወረድን ወይ ባድመን ለእኛ አላስወሰንን ወይ አሰብን አልተረከብን.. በዚህ መሰረት ምንም ላላመጣልን ጦርነት ወንድሞቻችንን አጥተናል ብሎ ነው የሚያስበው አንባቢ። ኮለኔሉ ያስቀመጧቸው ማስረጃዎች እንዴት ሊገቡን ይችላሉ?
#የባድመ ጉዳይ፦ ባድመ ለእኛ ተወስኗል ተብሎ ህዝቡን አደባባይ አስወጥቶ በማስጨፈር የዓለም መሳለቂያ አድርገው ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ተሰርቷል ይላሉ። ይህንን ያለው ደግሞ መለስ ሳይሆኑ ሌላ ሰው ነው ይሉናል። ፀሃፊው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በታሪክ ትልቅ ቦታ ኖሮት ነገር ግን ያን ያክል አልተወሳም የሚል አቋም እስካላቸው ድረስ ባድመ ለእኛ ተወስኗል ያለውን ሰው በግልፅ ተናግረው ሰውየው መልስ ቢሰጥበት ታሪክ ነው እና ሁሉን እንደ ታሪክነቱ አንባቢው ተረድቶ ያልፈዋል። እውነቱም ለታሪክ ይቀመጣል። ያንን ግን በፅሁፋቸው አላስቀመጡትም።
=የአሰብ ጉዳይ፦ የፀሃፊው የአሁኑ አቋማቸው አሰብ የእኛ እንደሆነና መመለስ አለባት የሚል አቋም አላቸው። ለጉዳዩ ደግሞ አቶ መልስ ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም። ይልቁንም በወቅቱ እሳቸዉ አሰብን በወታደራዊ ሃይል ለማስመለስ ሞክረን አልቻልንም ብለዉ ሲናገሩ አንድም ጀኔራል ወይም የጦር አዛዥ ወይም በዚያ ቦታ የነበሩ የፓርቲዉ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዳቸዉም ለማስተባበል አለመሞከራቸዉ የመለስን አቋም ትክክለኛነት የሚያሳይ ነዉ፡ ብለው ፅፈዋል። ይህንን ማወቅ ከቻሉ በጦርነቱ ወቅት የእኛ ወታደሮች የጦር የበላይነት ተቀዳጅተው ኤርትራ ድምበር ገብተው ከፍተኛ የመደራደር አጋጣሚ ይዘው ጦርነቱን እንዲያቆሙ ያዘዘውን አካል ስለምን ለአንባቢ ነግረው ምላሽ እንዲያገኝ አላደረጉም?
በሌላ መልኩ
መለስ አሰብን ለማስመለስ በነበራቸዉ ፍላጎት መሰረት ለሰራዊቱ አዛዦች እንዲተገብሩት ትእዛዝ መስጠታቸዉንና ሰራዊቱ ግን ሞክሮ ለግዜዉ እንዳልተሳካለት በገለጹበት ወቅትም ይህንንም ያስተባበለ አንድም ጄኔራልና ኮሎኔል አልነበረም" ይሉናል። ይሄ ደግሞ የባሰ ግራ ያጋባል። በእልህ አስመራ ደረሰን የኢሳያስን ጆሮ ይዘን እንመጣለን ብሎ ግፋ በለው ሲል የነበረ የኢትዮጵያ ሰራዊት ተመለስ ተብሌ ወሽመጡ እንደተቆረጠ ነበር እስከ ዛሬ የተፃፉ መፀሃፎች የነገሩን። እና እንዴት ሆኖ ነው?
"መለስ ጄኔራሎቹን አማክረዉ ወደፊት ለመግፋት አንደማይችሉ መልስ ከሰጡዋቸዉ በኋላ ነዉ ዉሳኔዉን የወሰኑት፡፡(ጦርነቱ እንዲቆም) ብለውም ይነግሩናል።" ይሄ ሌላ ማጠናከሪያ ነው።
=የጦርነቱ ድንገተኛነት ፦ እዚህ ላይ አገም ጠቀም አይነት ትንታኔ ነው የሚሰጡት። አንደኛው ጦርነቱ ድንገት መጣብን ማለት ለማንኛውም ጦርነት ማለትም ጠላት አለ ተብሎ ነወይ የአንድ ሃገር ጦር ዝግጁ የሚሆነው ብለው ይወቅሱና እንደገና ኤርትራ ልትወረን የምትችልበት አንዳችም ምክንያት የለም ከሚል እሳቤ ነው ብለው ነገሩን ሊያመጣጥኑት ይሞክራሉ። በዚያውም "ኤርትራ ልትወረን ነው" ብሎ የተናገረን አንድ ሰው "ትምክህተኛ ነህ" ተብሎ ከስራ እንደተባረረ ነግረውን አንባቢውን ያምታቱል።
በሌላ በኩል
መከላከያ ሃይላችን የራሱ ዶክትሪን የሌለው ዘመናዊ መሳሪያ ያልታጠቀ እና ገና ራሱን እያደራጀ ባለበት ወቅት ነው ወረራ የተፈፀመብን ይሉና ዝቅ ብለው ደግሞ ኤርትራ ስለ እኛ የተሳሳተ ግምገማ በመያዟ ነው የተሸነፈችው ይላሉ። መከላከያችን ራሱን ገና እያደራጀ ከነበረ የኤርትራ ግምገማ ትክክል ነበር ማለት ነው። ለውጤቱ ምክንያቱ የራሳቸው ድክመት አልያም የኤትዮጵያውያን ጀግንነት ነው የሚል ድምዳሜ መሰጠት ነበር ባይ ነኝ። እዚህ ላይም አንባቢ ግራ ይገባዋል።
ሌሎች የሚያወዛግቡ ሃሳቦች
#እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ የኤርትራ ህዝብም ሳያስበው ነው ወደ ህዝበ ውሳኔ የገባው ይሉንና ቀጥለው ሻቢያ አስመራን ከተቆጣጠረ ከሁለት አመት መኋላ ሁለት ዓመታት ነጻነቱን ሳያዉጅ የቆየዉም የኢህአዴግን ፈቃድ ለማግኘት ብሎ ሳይሆን ለሪፍረንደሙ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ግዜ ስላስፈለገዉ በራሱ ምክንያት ነዉ። የኤርትራ ህዝብም አበረው በዝግጅቱ ተካተው ነው የተፃፈው
#/ል ተወልደ ገ/ተንሳይ በፃፉት መፀሃፍ የጦርነቱን ድንገተኛነት የፃፉበትን መንገድ እንስተው የራሳቸውን አቋም አለመፃፋቸውን ይወቅሳሉ። ነገር ግን ኮለኔል አስጨናቂ ራሳቸው ስለ አሰብ እና ባድመ ጉዳይ በወቅቱ የነበራቸውን የግል አቋም ትንፍሽ አላሉም። እና ስለምን ሌላ ሰው መውቀስ አስፈለጋቸው?
#ጦርነቱ እንዲቆም ያደረጉ ግለሰቦች ኢህዴግ ውስጥ ነበሩ። ብለውን ጦርነቱ እንዲቆም መለስ ሳይሆን ያደረጉት ድርጅቱ ነው ባሉበት አንደበታቸው ከአይደር ትምህርት ቤት ጭፍጨፋ በኋላ ለኤርትራ ሽንጣቸውን ገትረው ተቆርቋሪ የሆኑ ሰዎች በድርጅቱ ውስጥ ነበሩ ያ ማለት ግን ድርጅቱ ለኤርትራ ይወግናል ማለት አይደለ ይሉናል። ግለሰብን ከድርጅት ለመነጠል ይሞክሩና ተንገዳግደው ድርጅቱና እና ግለሰቦችን ይቀላቅሉታል።
ሲጠቃለል
የአቶ መለስ ዜናዊን ስም መገንባትና ጦርነቱ በእኛ ድል አድራጊነት እንደተጠናቀቀ እንድናምን የተፃፈ ነው የሚመስለው።
እነዚህ ጉዳዮች በቀጣይ ፅሁፎቻቸው ግልፅ ያደርጉልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። (የእኔ የአረዳድ ችግር ከሆነም አፉ ይሉኛል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ)

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me