Search This Blog

Sunday 30 July 2017

ደረቅ ጭንቅላት እንጂ ደረቅ አፈር የለም

መቀሌ ነው አሉ። አንድ አውደ ጥናት ተዘጋጅቶ አንድ ፕሮፌሰር ጥናት ያቀርባሉ። ጥናቱ እፀዋት ላይ ያተኮረ ሲሆን ፕሮፌሰሩ "የግራር ዛፍ ችግኝ ችግር ስላለብን በቀላሉ ማብቀል(ማባዛት) አልቻልንም" ብለው ይናገራሉ። በአውደ ጥናቱ የተጋበዘ አንድ አርሶ አደር እጁን ያወጣና እሱ በጣም ቀላል ነው እኔ ላሳያችሁ እችላለሁ ብሎ ይናገራል። ፕሮፌሰሩ አርሶ አደሩን ምን ታውቃለህ ዝም በል አይነት ንግግር ይናገሩታል። እልህ የያዘው አርሶ አደር
"መኪና መድቡና እኔ ማሳ ድረስ ይዣችሁ ልሄድ" ብሎ ይከራከራል። ተፈቅዶለት የአውደ ጥናቱን ተሳታፊዎች ጭምር ይዘው ወደ ማሳው ያመራሉ። አርሶ አደሩ ግራሩን ያራባበትን መንገድ በተግባር እያሳየ ገልፃ አደረገላቸው። በዚህ ግዜ ፕሮፌሰሩ የሚገቡበት ይጠፋቸዋል። በዚህ የተበቃሳጨው አርሶ አደር
"ደረቅ ጭንቅላት እንጂ ደረቅ አፈር የለም" ብሎ ፕሮፌሰሩን አስገባላቸው። ይህንን የነገሩን የአውደ ጥናቱ ተሳታፊ የነበሩ ናቸው።
እነ ዶክተር ፍቀደ አዘዘ በአንድ ወቅት ለጥናት ወደ ሰሜን ሸዋ ሄደው ይመስለኛል ለጥናቱ አርሶ አደሮች ይሰበስባሉ። " እንግዲህ ለጥናቱ ሰዎች ስንመርጥ 'በራንደም ሳምፕሊንግ' ነው።ከእናንተ ውስጥ ዝም ብለን አንዳንድ ሰው እንዳገኘን እንመርጣለን" ይሏቸዋል። አንዱ አርሶ አደር
" እና በብድግ ብድግ መረጣ ነው አትሉንም ወይ?" ብለው ተናግረው ይህንን ቃል ወደ ቋንቋው አስገብተው ሲጠቀሙበት እንደነበር የፎክሎር መምህራችን ሲያስተምረን ነግሮናል። ምን ለማለት ነው ማህበረሰቡ ጋር ትልቅ እውቀት አለ። ተማርን ብለን በያዝናት ወረቀት ከምንኮፈስ ለማህበረሰቡ እውቀት እውቅና እየሰጠን መስራት ይኖርብናል። አርሶ አደሩ ጋር ተዝቆ የማያልቅ እውቀት አለ። ከአንድ የህክምና ዶክተር በተሻለ የባህል መድሃኒተኞች ስለ በሽታ እና መድሃኒት የተሻለ እውቀት አላቸው፣ ከታሪክ ባለሙያዎች ባልተናነሰ መልኩ ሽማግሌዎት የማያልቅ ታሪክ ያውቃሉ፣ ከግብርና ባለሙያ በተሻለ አርሶ አደሮች ስለ ምርት እና አፈር ምንነት ያውቃሉ። ልየነቱ ቀለም የማወቅ እና ያለማወቅ ጉዳይ ካልሆነ በቀር።

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me