Search This Blog

Sunday 30 July 2017

ብሽቅ!!!!!


እኛ እርግማን ያለብን ይመለኛል። "መቼም ሰው አትሁኑ" የሚል ከባድ እርግማን፦እርግማኑ መሬት ጠብ የማይል ሰው የረገመን እርግማን። ወይ እንደ ናይጄሪያውያን ለምንፈልገው አገልግሎት "ሃላል" ገንዘብ አምጡ ተብለን በይፋ አልሰጠን ወይ ደግሞ "ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመከላከል" እያልን መደስኮራችንን አልተውን አፋችን እና ልባችን ተለያይቶ እየኖርን ነው። ሰው የሚያወራውን የማይኖርባት፣ የተፃፈ የማይተገበርባት፣ ግብረ ገብነት ስሙ ሳይቀር የጠፋበት ዘመን (በእርጥ ሃገር ነው) ላይ ደርሰናል። ሰሞኑን የቀድሞ አስተማሪየን አግኝቼው ስለ ሃገራችን ጉዳይ የተወሰኑ ነገሮችን ስናወራ የነገረኝ ነገር በጣም አስደነገጠኝ። ሰውየው ከውጭ ሃገር በርካታ ገንዘብ ይዞ ይመጣል። አንድ ከተማ ውስጥ (ቦታውን እንተወው) ትምህርት ቤት ልስራና ወላጅ እና አሳዳጊ የሌላቸውን ህፃናት ማደሪያ እና ምግባቸውን ችየ ላስተምር ብሎ ጥያቄ ያቀርባል። (በእርግጥ ሰውየው የግለሰብ ቤት ተከራይቶ ይህንን እያደረገ ነው።ለማስፋፋት አስቦ ነው) "ቦታ እንዲፈቀድልህ ይህንን ያክል ገንዘብ አምጣ" ተባለ። እያዘነ "እኔ እኮ መተውም እችላለሁ" ነው ያለው። ይታያችሁ እንግዲህ ይሄ ሰው ልነግድብት ቦታ ስጡኝ አላለም፣ ፋብሪካ ልገንባም አላለም፣ የክፍያ ትምህርት ቤትም አይደለም ልገንባ ያለው። "የተቸገሩ የሚማሩበት የነፃ ትምህርት ቤት ልገንባ" ነው ያለው። ምን አይነት ጭንቅላት ያለው ሰው ነው ለዚህ ለበጎ አድራጎት ተግባር ገንዘብ ሰጠኝ የሚለው ልትሉ ትችላላችሁ። "የጭንቅላቱን አይነት እናንተ ስም አውጡለት" እንልና "ጭንቅላቱ ይፍረስ" ብለን ተራግመን እናልፋለን። (ከዚህ በላይ ምን አቅም አለንና?) አስተማሪየ ይህንን ሲነግረኝ እንባ እንባ እያለው ጭምር ነበር። እንኳን እሱ በማስተማር ተግባር ላይ እያለ እኔ ራሱ ይህንን ስሰማ የተሰማኝን መጥፎ ስሜት ብገልፀው አሸባሪ ተብየ ልፈረጅ እችላለሁ። በደማሚት ነበር ማፍረስ የምትሉት መስሪያ ቤት አጋጥሟችሁ ያውቅ የለ? ልክ እንደዚያ የገንዘብ ጠያቂውን ጭንቅላት ማፍረስ ነበር የታየኝ። ይሄንን ባደርግ በርካታ መማር ያልቻሉ ህፃናት አንድ ጋሬጣ ነቅየላቸው ትምህርት በነፃ ያገኛሉ፣የተመቻቸም ህይወት ይኖራሉ ብየም አሰብኩ። እንዲህ ያለ የቀን ጅብነት ከየት ወረስንው? እና ታዲያ ከዚህ በላይ እርግማን አለ?

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me