Search This Blog

Sunday 30 July 2017

"አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት እያድር ይፋጃል እንደ እግር እሳት"

"አባቴ ሰይጣንን የሚያመልክበት ጎጆ ቤት ነበረው። የሆነ ወቅት ላይ ቤቷ ፈረሰች። ሰይጣንም አባቴን ቤቴን ካልሰራህልኝ ደመራን አላሳልፍህም እግድልሃለሁ አለው። አባቴ ነገሬ ሳይለው ተወው። እንደተባለው አባቴ ሆዴን ወጋኝ ብሎ ከዚህ ዓለም ተለየን። በዚያው ሳምንት እናቴም ሆዴን አመመኝ ብላ ለሞት በቃች። እኔ፣እህቴ እና ወንድሜም የትም ተበተንን። የምንበላው እና የምንለብሰውን ሰዎች እየመፀወቱን በነፍስ ለመቆየት ያክል እንኖራለን" አለች እና እንባዋ ዝርግፍ ብሎ ወረደ። ያሳዝናሉ። ኑሯቸው ከመቃብር በታች የሆነ ያክል ነው። እነዚህ ልጆች የሚኖሩት ከደብረ በረሃን በግምት 25ኪ.ሜ ከምትርቅ ቀይት ከምትባል ከተማ ውስጥ ነው። ምግባቸውን መምህራን በየተራ እያመጡ ይሰጧቸዋል። ለዚያውም ካልሰለቹ!! ከደሞዛችን ያዋጣናትን እና Hirut Negesue ሂሩት ነገሰ ሰብስባ የላከችልንን ገንዘብ ከፋፍለን የ2ወር ቀለብ እንዲገዛላቸው አደረግን። ሆድ እየጮኽ ትምህርት እና ለውጥ እንዴት ሊታሰብ ይችላል? ልጆቹ ይቺ ተደረገችልን ብለው ፈጣሪ ከሰማይ የወረደላቸው ያክል ተደሰቱ። አንጀት ይበላሉ።
ጓደኞቻችን Misahun Negash እና ይርጉ ኃይለማሪያም የመለመሏቸው ሌሎች ችግረኞች ቤት ሄድን። ከዚችው ከተማ * ኪ.ሜ አካባቢ ወደሚርቅ እና አዲስጌ ወደሚባል ቀበሌ። እዚህም ሌላ ችግር በሰዎች ላይ አፉን ከፍቶባቸዋል። እዚህ ቤት አንድ ልጃቸው ችግር አስመርሯት ወልዳ አራስ ልጇን ትታ በገመድ ታንቃ ሞተች። እናት ከሃዘን እና ከችግር ጋር የልጅ ልጇን ማሳደግ ተፈረደባት። የወላድ አንጀት ይሄን እንዴት ይቻል?
"አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት
እያድር ይፋጃል እንደ እግር እሳት" የሚለውን ግጥም አስታወስኩትና አጥንቴን ሰርስሮት ገባ። ችግር እና መጎሳቆል ሰው ፊት ላይ ሲነበብ ማየት ህመሙ ከተቸገሩት ሰዎች የሚተናነስ አይመስለኝም። ቤት መኪና ምናምን መመኘቴን እርግፍፍ አድርጌ ተውኩት። የችግራቸውን ሁኔታ አንድ በአንድ ነግሬ ሌላ ሃዘን እንድጨምርባችሁ ስለማልፈልግ ልዝለለው። ብቻ እዚህ ቤትም ትንሽ ነገር ተደረገችልን ብለው እንባ ተናነቃቸው። ገንዘቡን ለመስጠት ስንሄድ የቀበሌውን አስተዳዳሪ እንዲገኝ አድርገን ስለነበር ነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የድጋፍ ፍቃድ እንዲሚሰጧቸው እና የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው እንደሚችሉም ቃል ገቡልን። እኛ በሰበሰብናት ሚጥጥየ ገንዘብ ሰዎችን ማነሳሳት መቻላችን ትልቁ ግብ አደረገን ወሰድንው። እዚያው ወረዳ ላይ ሙሽ የሚባል ቀበሌ ላይም ሌላ ችግር ያነወዘው ቤተሰብም ጎበኘን። የሚያሳዝነው ሁሉም ቤት ልጆቹ ሲመረጡ የአካል ጉዳት እና ሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮች ያለባቸው ልጆች ነበሩ። የሆነው ሆኖ ባይጠቅምም ወገን አለን ብለው እንዲያስቡ ያደረግናቸው ይመስለኛል። እኛ ገንዘብ ኖሮን አይደለም ይህንን ያደረግንው። ብዙዎቻችን ከቤት ኪራይ የሚያልፍ ደሞዝ የለንም። ስንሰባሰብም ከደሞዛችን በወር 1መቶ ብር ብንለግሳቸው ብለን ነው። ይበዛብናል ሳንልስ እንቀራለን!? ከሁሉ ነገር የሚበልጥ ሰውን የመርዳት ወኔ ግን ነበረን። እነዚህ ልጆች ትንሽየ ከተማ ውስጥ ለቤት ኪራይ በወር 30 ብር የሚሰጣቸው ሰው ከምንም በላያቸው ነው። ከተማ ውስጥ ጎዳና የወጡ ሰዎች እኮ በቀን እጁን የሚዘረጋላቸው ሰው አያጡም። ገጠር ውስጥ ያሉት ግን ስለመኖራቸውም አይታወቁም። ተራፊ የሚሰጣቸው አይኖርም። የአብዛኛው ህዝብ አኗኗር ከዚህ ጋር የሚቀራረብ ቢሆንም እጅግ የባሱትን ማየት ሁሉ ነገር ውሸት መሆኑን ማንም ሰው ይረዳል። በቃ አሁንም ድሃ ነን። እልም ያልን ድሃዎች። የሆነው ሆኖ ቀጣይ ፕሮግራም ይኖረናል። ባናግዛችሁ እንኳ የልጆቹን አኗኗር አይተን በሃሳብም ቢሆን እንረዳዳለን የምትሉ ካላችሁ ቀጣይ ላይ አብረን ተጉዘን ኑሯቸውን አይተን መመለስ እንችላለን። ከአዲስ አበባ ደርሶ መልስ 120 ብር ቢፈጅ ነው። ሰዎች ያድርጉ ከማለት እኛም ትንሽየ ነገር ብናደርግ የአዕምሮ እርካታ ነው፤የማህበረሰብ ድጋፍ ነው፣የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ነው፤ህዝብ መውደድ ነው፤ህዝብን መውደድ ደግሞ ሃገርን መውደድ ነው። ህዝባችንን ሳንወድ እና ማገዝ እየቻልን ባናግዛቸው ሃገሬን እወዳለሁ ብንል ትርጉሙስ ምንድነው? አድራሻችሁን ብታስቀምጡልን አንድ ቀን በሚኖረን የደርሶ መልስ ጉዞ አብረን መጓዝ እንችላለን!!
#ሼር ብታደርጉና ለወዳጆቻችሁ ብታደርሱልን ደጋግ ሰዎችን እንድናገኝ ያግዘናል። እናንተም ይህንን ስታደርጉ ሰዎቹን እንደረዳችኋቸው ቁጠሩት።
መልካም ግዜ

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me