Search This Blog

Sunday 30 July 2017

CIA የሚባለው አሸባሪ

CIA የሚባለው አሸባሪ ይቅርታ የአሜሪካ የስለላ ተቋም አይነውሃቸው ያአላማሩትን ሃገሮች በዚህም በዚያም ብሎ የጦርነት አውድማ ያደርጋቸዋል። ዓለም ላይ የሚፈጠሩ ግጭቶች ሁሉ ላይ እጁ ቢኖርበትም ሌላው ቀርቶ ሊቢያን እና ኢራቅን እንኳ ትተን ሶርያን እናስባት። የሶሪያን ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድን የኬሚካል የጦር መሳሪያ አለህ በሚል በኦባማ አስተዳደር ጥርስ ተነከሰበት። የሃገሪቱ በአሜሪካ ጥርስ ውስጥ መግባት የኬሚካል የጦር መሳሪያሽን አስወግጂ ከሚል በሉዓላዊት ሃገር ላይ በመግባት ወደ የሃገሪቱን ፕሬዝዳንት ከስልጣን ማውረድ ሃሳብ ተሸጋገረ። ይሄው ስድስት አመት ሆነ ሱሪያ ሰላም አጣች። የሚያማምሩ እና ጥንታዊ ከተሞቿ ወደሙ። የሃገሬው ህዝብ ግማሹ ተሰደደ። በሚሊየን የሚቆጠሩ ተገደሉ። ይህ የሆነው በበሽር አላሳድ ላይ እንዲነሱ የሰለጠኑ አማፅያን እና አይኤስም ጭምር ነው። አልጃዜራ እና ሌሎች የተወሰኑ የመገናኛ ብዙሃን አይኤስ የተባለውን አሸባሪ ቡድን የፈጠረችው እና ይልሰለጠነችው አሜሪካን ናት ስልጠናውን የወሰደው ደግሞ ቱርክ ውስጥ ነው ሲሉ አጋለጡ። ይህንን ጉዳይ ትራምፕ ለምርጫ ቅስቀሳቸውም ተጠቅመውበታል። አይኤስን የፈጠረው ኦባማ ራሱ ነው ብለው ቃል በቃል ተናግረዋል። በእርግጥ ምንም የማታውቀው ሃገራችን እንኳ የእነዚህ ሽብርተኛ ቡድኖች ሰላባ ስትሆን አሜሪካ ግን በፍፁም አልተነካችም። አሜሪካ ያልተነካችው ውለታን ላለመብላት ይመስላል። ዞር ትልና አሜሪካ ለሽብርተኞች ድጋፍ እያደረገች ሽብርተኝነትን እንዋጋ ትልሃለች። 6ዓመት ለዘለቀው የሶሪያ ጦርነት በአንድም በሌላ መልኩ አሜሪካ እሳት ስትቆሰቁስ እንደነበር ግልፅ ነው። ይባስ ብሎ አሜሪካ በሽብር ቡድኑ ላይ የአየር ጥቃት ፈፀምኩ ባለች ሰሞን ቡድኑ ተጨማሪ ይዞታዎችን በቁጥጥሩ ስር ሲያውል ነበር። አሜሪካ የአየር ጥቃት የምትለው ለአሸባሪ ቡድኑ መሳሪያ የማቀበል ተግባሯን ነው የሚሉም አሉ። 6ዓመት በፈጀው የእርስ በእርስ ጦርነት ለአሜሪካ በጦር መሳሪያ ሽያጭ ተጨማሪ ገቢ ሲሆናት አሸባሪ ቡድኑ ከሶሪያ ያገኘው የነበረውን ነዳጅ በቱርክ በኩል በውል አትርፋበታለች የሚሉም አሉ። ነዳጅ ትገዛለች የሄደባትን ብር የጦር መሳሪያ ሸጣ ትመልሰዋለች ነው ነገሩ። በአለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉት CNN እና BBC የመሳሰሉ መገናኛ ብዙሃን እንኳ ይቺን ትንፍሽ አይሉም። ይልቁንም የሶርያን ግጭት አድሏዊ በሆነ መልኩ ነበር ሲዘግቡት የነበረው።
ሰሞኑን ዶናልድ ትራም CIA ለሶሪያ አማፂዎች የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲያቆም ወሰኑ የሚለው ዜና የእስካሁኑን ቁማር ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። አሜሪካ አማፂዎቹን ትደግፋለች የሚል ይፋዊ መረጃ ሳይወጣ ኖሮ የትራምፕ ውሳኔ ይህንን እውነት እርቃኑን ያስቀረ ነው። አማፂዎቹ አንድም አይ ኤስ ነው አንድም የኩርድ ታጣቂዎች አልያም ደግሞ የፒሽመርጋ ታጣቂዎች።(ኤራቅን ጨምሮ) እንደሚታወቀው በሶርያ ጉዳይ ሩስያ ገብታ ሶሪያን ከጡንቻ መፈተሻነት በተወሰነ መልኩ ታድጋታለች። አሜሪካንም ረገብ ያለችው ሩስያ ከአሳድ ጎን በመቆሟ ነው። በንፁሃን ሞት እና ስደት ላይ እቃ እቃ ስትጫዎት የነበረችውን አሜሪካ ይህ የሩስያ ከአሳድ ጎን መቆም እጅጉን አስቆጣት። ወደ ማዕቀብ መጣልም ወሰዳት። በዩክሬን ጉዳይ ንፋስ ገብቶበት የነበረው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት የባሰ ተሸረሸረ። ሩስያም በአቋማ ፀናች። በነገራችን ላይ የአሜሪካ ፍላጎት የሶርያውያንም ፍላጎት ቢሆን ኖሮ አሳድ ለአንድ ሳምንት እንኳ ስልጣን ላይ ባልቆየ ነበር። ስለዚህ ሰውየው የህዝብ ድጋፍ አለው ማለት ነው። አምባገነን መሪዎች ትንሽ ችግር ሲገጥማቸው ህዝቡ አባብሶ ገደል ይከታቸዋል እንጂ ህዝብ መቼም አይደብቃቸውም። ለማንኛውም ከእነ አሜሪካ በኩል ያለው የሃይል ሚዛንን ሊገዳደሩት የሚችሉት ሩስያና እና ቻይና ብቻ ናቸው። በቅርቡ የሰሜን ኮርያ ጉዳይ ደግሞ ሌላ አሰላለፍ አመጣ። አሜሪካ ሰሜን ኮርያ የኒውክለር መርሃ ግብሯን ካላቆመች ወታደራዊ እርምጃ ሁላ ልወስድ እችላለሁ አለች። ቻይና በጉዳዩ ዙሪያ ስትጠየቅ ችግሩን በሰላም እንዲፈታ የበኩሌን እወጣለሁ ብላ ወደ ንግዷ ተመለሰች። የቻይናን ድጋፍ በዚህ መልኩ ያጣችው አሜሪካ የሩስያን ከጎኗ መሰለፍ እንዴትም ልታገኝ አትችልም። በዩክሬን እና ሶርያ ጉዳይ ሆድ ተዋጥተው ትብብሩ እንዴት ሊታሰብ ይችላል? አሜሪካ በሌለ ነገር ኢራቅን ለአሸባሪ መፈንጫ እንዳደረገቻት ሁሉ ሰሜን ኮርያንም ልክ ማስገባት ትፈልግ ነበር። ያንን ለማድረግም የተለያዩ ማስፈራሪያዎችን አድርጋለች። አንዳንድ ባለሙያዎች የሰሜን ኮሪያን የሚሳኤል ጥቃት አሜሪካ የመመከት አቅም የላትም ሲሉ አሜሪካንን ሳያስደነግጣት አልቀረም። አሜሪካን ከደቡብ ኮርያ ጋር በጀመረችው የጦር ልምምድ እና "ወዳጄቼን ከሰሜን ኮርያ ጥቃት እከላከላለሁ" ዘመቻ ደቡብ ኮርያውያንን አስቆጣ። ደቡብ ኮርያውያን በሰሜን ኮርያ ልታስፈጁን ነወይ ብለው ተቃወሙት። ያለው አማራጭ ሁለቱን ኮርያዎች ነገሩን ወደ ሰላማዊ ትብብር አዙሩት ሆነ። አሜሪካ ባትፈራ ኖሮ ኢራቅ ውስጥ ገብታ የሉዓላዊቷን ኢራቅን መሪ በዚህ ሰዓት ሃገርክን ለቀህ ካልወጣህ ብላ ኤራቅን የጦር ቀጣና እንዳደረገቻት ሁሉ ሰሜን ኮርያ ውስጥም ገብታ ያንን ጎረምሳ መሪ በ24ሰዓት ካልወጣ አልያም በ48 ሰዓት የኒውክለር መረሃ ግብሩን ካላቆመ ብላ አስፈራርታ ሃገር ታፈርስ ነበር። ዛሬ የሰሜን ኮርያ ጡንቻ ይህንን እንድታደርግ አላስቻላትም። በሶሪያ ጉዳይ ወደ አዲሱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የተላለፈው ቅራኔ ሩስያን በሰሜን ኮርያ ጉዳይ ጥጓን እንድትይዝ አደረጋት። ይህንን የተረዱት ትራምፕ ጀርመን ከተካሄደው የቡድን 20 ሃገራት ስብሰባ ጎን ለጎን ከፑቲን ጋር ሲወያዩ ለሶርያ ሰላም እንሰራለን ሲሉ ተስማምተዋል። ወዲያው ነው ትራምፕ CIAን የአማፂዎችን መደገፍ እንዲያቆም የወሰኑት። የዓለም መገናኛ ብዙሃን ከውይይታቸው ውስጥ መርጠው ሲያራግቡት የነበረው የሩስያን በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ መግባት ጉዳይ ነበር። ከትራምፕ ጋር ቃለመጠይቅ ያደረጉ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ትራምፕን ወጥረው ይጠይቋቸው የነበረው ይህንን ነው። ስለምን ለሶርያ ሰላም ከሩስያ ጋር እንሰራለን አሉ የሚለውን ማንሳት አልፈለጉም? አንደኛ ይሄ ውሳኔ የአሜሪካንን ሽንፈት የሚያሳይ ነው። ሁለተኛ የሩስያን ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያንፀባርቅ ነው። ትራምፕን የማይወዱት የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እንኳ ሃገራቸው እጅ ሰጠች እንዳትባል ይመስላል ይቺን የዘለሏት። ትራምፕ ለሶርያ ሰላም እንሰራለን ሲሉ ጦርነቱ እንዲያበቃ ከሩስያ ጋር በሩስያ አካሄድ እንሰራለን ነው። ቻይንኛው ደግሞ በሩስያ መሸነፋችንንን አመነናል ነው። አሳድን ከስልጣን እስከ ማውረድ የደረሰ ሃሳብ በሩስያ ተበላ። ይህ የአሜሪካ ልስላሴ ወይም የፓለቲካ አክሮባት ልትጋፋት ያልቻለችውን ሰሜን ኮርያን ለመጣል ከሩስያ ጋር ስምም መሆንን ያለመ ይመስላል። ቻይናን እና ሩስያን ከጎኗ ካላሰለፈች ደግሞ ይሄ ነገር አይሳካም። ቻይና ደግሞ ለእንዲህ አይነት እብሪት የሚመስል አካሄድ እጇን አታስገባም። የቻይና ጨዋታ ከሌሎች ሃገራት ጋር ቢዝነስ እና ቢዝነስ ብቻ ነው። ሩስያም በሃሳብ ማፈንገጥ ከጀመረች ከርማለች። በሰሜን ኮርያ ጉዳይ ከአሜሪካ ጎን ትሰለፋለች ማለት ዘበት ነው። የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ ነው ነገሩ። እንደ አሜሪካ ተንኮል ቢሆን ሩስያ በኢኮኖሜ ድቅቅ ብላ ነበር።ይቺን ረስቶ ማን ሞኝ አለ ከአሜሪካ ጎን የሚሰለፍ። የሆነው ሆኖ ፑቲን የአማሪካንን የጥቅም ፓለቲካ ተረድተው የሃይል ሚዘኑን በዚሁ እንዲቀጥል ካደረጉ የአሜሪካ በጥባጭነት ይገታና ዓለም ሰላም ወደ መሆን ታዘነብላለች። ሶርያና ኢራቅ ውስጥ የፈለፈለቻቸው አማፅዎች እና አሸባሪዎች እንዲጠፉ አሜሪካ እና የስለላ ተቋሟ ሃይ ባይ ያስፈልጋታል። ሃይ ባዩዋ ደግሞ ሩስያ ብቻ ናት። ብራቮ ፑቲን

No comments:

Post a Comment

Translate

About Me